የሰው ልጅ ኑባሬ ቅኝት በገ/ክርስቶስ ደስታ መንገድ ስጡኝ ሰፊ የግጥም መድብል
አኅፅሮተ-ጥናት: ይህ ጥናት በገ/ክረስስቶስ ደስታ (1998) “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በተሰኘው የግጥም ስራ የሰው ልጅ ኑባሬ (Being) በምን መልክ ተገለፀ በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ በዚህ ቅኝት በገ/ክርስቶስ የተለያዩ ግጥሞች መካከል ትስስር በመፍጠር ለሰው ልጅ ኑባሬ መገለጫ ሆነው የቀረቡ መሰረታዊ ህግጋቶችን (categories) መርምሮ ያወጣል፤ በህግጋቶች ኑባሬ ስለተገለጠበት ሁኔታ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ለዚህም ሲባል አንድምታ (hermeneutics) የደራሲው ሀሳብ ምልዓት (content) ሳይዛባ በግጥሞች ውስጥ ባሉ ቃላት፣ በስንኞች እንዲሁም በተለያዩ ግጥሞች መካከል ትስስር በመፍጠር ትርጉም ለመስጠት በማስቻሉ የጥናቱ ስነ-ዘዴ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በዚህ ስነ-ዘዴ ከገ/ክርስቶስ 60 አካባቢ ከሚሆኑ ግጥሞች ውስጥ ከጭብጣቸው አንፃር ለጥናቱ ያስፈለጉት ትርጉምና ትንተና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት፣ ለገ/ክርስቶስ ኑባሬ በመሰረታዊነት ግላዊ ሲሆን በቅይይረዊ ጊዜ (temporal time) እና ህላዌ-ስፍራ (existentialle space) መሳክነት (continuum) የሚገነባ የመኖራችን ማሳያ መሆኑን ጥናቱ በግጥሞቹ የጭብጥ ትረጉም አሳይቷል፡፡
ቁልፍ ቃላት:- ህላዌ፣ ስፍራ፣ ኑባሬ፣ ገ/ክርስቶስ ደስታ፣ ጊዜ
The ‘Being’ of Man in Gebre-Kiristos Desta’s Anthology of Poetry
Abstract: This study investigates how the ’Being' of man is represented in Gebre-Kristos Desta’s (2005) ’Menges Situgn Sefi’ (Give me vast pathway) Anthology of Poetry. The study has identifed fundamental categories which Gebre-Kirstos has provided implicitly or explicitly as the basis of the fundamental ontology of humans. In light of these categories, the study has provided meaning to how Gebre-Kistos understood the the ‘Being’ of humans. A hermeneutic reading of the texts in general and the poems in particular has been employed to interpret the fundamental nature of the Being of humans as represented in the poems.
Keywords: Being, Existence, Gebre-Kistos Desta, Space, Time
1 PhD Student, Doctoral School of Philosophy, University of
Szeged, Hungary
Lecturer, Department of Political Science and International Studies, Bahir Dar
University, Ethiopia
Email: belayneh3415@gmail.com
መግቢያ
ይህ ጥናት በዋናነት በገ/ክርስቶስ ደስታ (1998) “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በተሰኘው የግጥም ስራ የሰው ልጅ ኑባሬ (Being) በምን መልክ ተገለፀ በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ገ/ክርስቶስ ደስታ በ1950ዎቹ በኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ከነበራቸው የኪነ-ጥበብ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ፈቃደ አዘዘ(2001)2 ገ/ክርስቶስን፣ “ግለኛ እና አዲስ የአሰነኛኘት ዘዴን በመከተል በኢትዮጵያ የስነ-ግጥም ባህል ውስጥ አዲስ ንቅናቄ የፈጠሩ ግጥሞቹና ቅኔዎቹ የአማርኛ ቋንቋን ጣዕምና ለዛ ቀላል በሆነ፣ ነገር ግን ቅኔዊ ውበትን በተጎናፀፈ የገለጣ ሀይል እስከ ባህላዊ ትውፊታችን ድረስ በመዝለቅ የኢትዮጵያውያንን ነፍስ የገለፀ ነው” ይለዋል፡፡ ብርሃኑ ገበየሁ (2001)÷ ስለ ገ/ክርስቶስ በሁለት ጥበባት ነፍስያውን መግለጥ ያቻለ፣ በቃላት ሚስል፣ በስዕል የሚተረክ፤ የዐማርኛን ስነ-ግጥም አቅጣጫ ለማስያዝ ከታተሩትና ከተቻላቸው መካከል አንዱ ስለመሆኑ ይስማማል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ዮናስ አድማሱ በገ/ክርስቶስ መንገድ ስጡኝ ሰፊ የግጥም መድብል ቅድመ-መግቢያ ላይ እንዲህ ሲል ገ/ክርስቶስን ይገልፀዋል፤
የማህበረሰቡ ነባር ስርዓት በአንድ የታሪክ ይሁን የኢኮኖሚያዊ-ማህበራዊ-ፖለቲካዊ ለውጥ የተነሳ እስኪለወጥ ድረስ ስርዓቱ ለሚመራባቸው ብዙ የተለያዩ እሴቶች፣ የእሴት ስርዓቶች፣ ትርጉሞችና የትርጉም እርከኖች እንዲሁም ማህበረሰቡ ተቀብሎ ለሚገዛባቸው “ቋንቋዊ ደንቦች” ተገዢ መሆኑን የተረዳ በዚህ መንገድ በጽምረትም፣ በስምረትም አንዳንዴ በተቃርኖ ለመጓዝ ፈቃድ ያለው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም እንዳለበት የተረዳ ይመስለኛል (ዮናስ፣ 1998፣ ገጽ 24)፡፡
ገጣሚ የሚፅፈውን ጉዳይ ከእመሃበ-አልቦ አያወርደውም፤ ገጠመኝ ካደረገው እውነት፣ ከአካባበቢው፣ ከሰማው፣ በሱ ከደረሰው በአዲስ መልክ ቅርፅ ያስይዘዋል እንጂ (ብርሃኑ ገበየሁ፣ 2001)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ፀጋየ ገ/መድን (1988) “ገጣሚ በግጥሙ ህይዎትን አትኩሮ ለመዝለቅ ኅሊናን በኅሊና የመፈተሸ ወጤት ናት” በማለት ይከራከራል፡፡ ገ/ክረስቶስ እንደገጣሚ ግጥሞች በቅርፅም ይሁን በይዘት በእራሱ የህይዎት ፈተሻ፣ እሱ የሚያውቀውን ከአካባበዊ ከቀስመው እውቀት ጋር በማቀዳጀት፣ ነገር ግን በእራሱ የአስተሳሰብ ዜዴ እንደቃኛቸው እሱ እራሱ ለድርሰት በነበረው አመለካከት እንዲህ ሲል ይመሰክራል፤
ደራሲ የሆነ ሁሉ ብዙ መፅሃፍትን ማንበብ፣ ማጥናት እንዲሁም እራሱ ከአካባቢውና ከኑሮው የሚቀስመውን እውቀት ልብ አድርጎ መመርመር፣ ሁለቱንም እያስተያየ ግን አንድ የግል የሆነ የአፃፃፍና የአስተሳሰብ ዘዴ መፍጠር እንዳለበት መገንዘቡ አይቀርም (ገ/ከርስቶስ፣ 1998፣ ገጽ 37)፡፡
2 ይህ ለገ/ክርስቶስ የተሰጠ አስተያየት ፈቃደ አዘዘ በ 2001 ዓ.ም. በአዲስ አባባ የጀርመን ባህል ማዕከል ለገ/ክርስቶስ መታስቢያ “ገ/ክርስቶስ ገጣሚ ወይስ ስዓሊ” በሚል በቀረበው ወይይት ለውይይቱ መክፈቻ ካቀረበው ንግግር የተወሰደ ነው፡፡
ዩናስ አድማሱ በበኩሉ የገጣሚ የግጥም ጥበብ ስልቱም ሆነ ይዘቱ ከገጣሚው ግለሰብ በፊት ባለው የማህበረሰቡ ቋንቋ እና ቋንቋው በተቃኘበት በባህል፣ በርዕዮተ-አለም፣ ብዙ የተለያዩ እሴቶችን፣ የእሴት ስርዓቶችን በልዩ ትርጉሞችና የትርጉም እርከኖች ተዋቅሮ ከቆየ ስርዓት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይከራከራል፡፡ ዮናስ በመቀጠልም በዚህ ተዋቅሮ በቆየ ስርዓት ማለትም የጥንቱኑ የምልክት፣ የፅንሰ ሀሳቦች፣ የእሴቶች ውቅር ውስጥ ገጣሚው እሱን ለመሰጠው፣ እሱ ለመረጠው ሀሳብ፣ እሱን ለቀሰቀሰው ስሜት የቋንቋው ደንብ በሚፈቅደው (አንዳንዴ ግድ በሚለው) መሰረት እራሳቸውን አሳልፈው በሰጡት መልሶ ባዋቀረበት መንገድ የእራሱን የግጥም ወጥነት ይይዛል በማለት ይተነትናል (ዮናስ፣ 1998)፡፡
የግጥም ስራ ገጣሚው እሱ ለመረጠውና እሱን ለቀሰቀሰው ሀሳብና ስሜት ቋንቋን ተጠቅሞ በግጥም ሲገልፅ የግጥም ቀስቃሽ ሀሳብ እና ስሜት በዘመን መንፈስና በማህበረሰቡ የባህል ስርዓት3 ከመቃኘትና ከመወሰን ያልፋል፡፡ ከዚህ ይልቅ የዘመኑን መንፈስና የጥንቱን የባህል ስርዓት እንደ አውድ (context) በመውስድ ለገጣሚያን እራስን ወይም “ሰውነትን” መጠየቅና ለዚህም መልስ መስጠት፣ በዚህ ሂደት የባህል ስርዓቱንና የዘመኑን መንፈስ በጥርጻሬ መጠየቅ፣ ለጥንቱ ወይም ለገዥው መንፈስ ተምሳሌቶች አዲስ ትርጉም መፈለግ ለገጣሚ ሁሉ የግጥም የይዘት መነሻ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ Heidegger (1962) እንዳመለክተው ሰው ስለሌሎች ሰቦች ይሁን ሰለለሌሎች በእሱ ዙሪያ ለሚገኙ ማህበራዊና ተፈጥሮዊ ነገሮች (ቁሶች) ወይም ክስተቶች የሚኖረው ስነ-ኑባሬዊ (ontology) አንድምታ መሰረቱ ሰው ስለእራሱ ከህላዌነቱ4 (existential) በመነሳት አስቀድሞ ከሚሰጠው ኑባሬ5 (Being) ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፤ “… therefore, fundamental ontology, from which alone all other ontologies can take their rise, must be sought in the existential analytic of Dasein (man)” (Heidegger, 1962, p. 32).
3 ባህል የሚለው የአማርኛ ቃል የእንግሊዝኛውን “culture” የሚል ቃል
አይተካም ሲሉ ምሁራን ይደመጣሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው የአማርኛው ቃል “ባህል” ትርጉም ውስንና ከፅንሰ-ሀሳብ አንፃር የእንግሊዝኛውን
culture ትርጉም አለመተካቱ አንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም ብርሃኑ ድንቄ (1987) “ሀሪሶት” የሚለውን ቃል ይጠቀማል፡፡
ከዚህ በተለየ እጓለ ገ/ዮሃንስ (1958) “ስልጣኔ” የሚለውን ቃል ይጠቀማል፡፡ ምንም እንኳን ባህል የሚለው ቃል የትርጉም
ውስንነት ቢኖርበትም በዚህ ጽሑፍ ለእንግሊዝኛው culture ምትክ ሆኖ ሰፊውን የማህበረሰብ ስርዓት የሚገልፅ ሆኖ ጥቅም
ላይ ውሏል፡፡ ባህል የአንድ ማህበረሰብ አባላት የተወሰነ ፊዚካላዊና ማህበራዊ እውነታ መገለጫ የሆኑ ስርዓቶችን (ማለትም
የማህበረሰቡን ቋንቋ፣ የጋብቻ ስርዓት፣ ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነቶች፣ ስነ-ጥበብ፣ ሳይንስና ሀይማኖትን) በውስጡ አቅፎ የያዘ
ነው፡፡ የአንድ ማህበረሰብ ቋንቋ የቃላት፣ ሀረጋት፣ ዓርፍተ-ነገሮች፣ ምልክቶች (signs) እና የአካል/የሰውነት እንቅስቃሴዎች
ስብስብ ነው፡፡ እነዚህ በአንድ ቋንቋ ውስጥ ተካተው የሚገኙ ስብስቦች ለማህበረሰቡ ባህል ጥቅል ስርዓቶች ውክልናዎች (symbols)
ናቸው (Lévi-Strauss, 1977/2001)፡፡
4 ሀልዎ (ዎት) ይሄሉ ሀለወ፣ ሀሎ ትርጉም፡- መኖር፣ መገኘት፣ መሆን፣ መፈጠር፡፡ ምሳሌ፡- እግዜአብሄር
አምጻኤ ኩሉ ዓለም እምኅበ ኢሀልዎ ኀበ ሀልዎ፡፡ ህላዊ (ዊት፣ ውያን፣ ያት) ትርጉም፡- የሚኖር፣ ነዋሪ፣ ኋኝ ምሳሌ፡ ነፍስሰሀላዊት
ይእቲ ወኢትትዌለጥ፡፡ ህልው (ዋን፣ዋት፣ሉት) ትርጉም፡- ያለ፣ የኖረ፣ የሚኖር ናባር፣ ቀዋሚ እውነት ምሳሌ፡-ፈጠረ ፍጥረት
ይኩን ህልወ መድኃኒን ዘህልው እመቅድመ ዓለም፡፡ ህላዌ (ውያት) መኖር፣ መኾን፣ አናዎር፣ ኑሮ፡፡ ምሳሌ፡- ንዜኑ ህላዌሁ
ለአብ ምስለ ወልዱ ወህላዌሁ በወወልድ መስለ አበሁ(ኪዳነ-ወልድ፣ 1948)፡፡
5 ኑባሬ መኖር ፣ መቀመጥ፣ ኗሪነት፣ አናኦር፣ ኖሮ፡፡ ነቢር (ሮት) (ነበረ፣ አው፣ ይነብር፣ ነበረ ይንብ(በ)ር)
ህልዎ፣ መኖር፣ መቆት፣ መዘግየት መቀመጥ ጉብ ጉች ማለት ዘርፈጥ ማለት፣ በወንበር ላይ ማረፍ፡፡ ነባሪ (ሪት፣ ርያን፣ ያት፣
በርት) የሚኖር፣ ነዋሪ፣ ነባር፣ ተቀማጭ ንቡር (ራን፣ራት፣ብርት) ያለ፣ የኖረ፣ የነበረ፣ የተቀመጠ፣ ቅምጥ፣ ጽሁፍ ንብረት
በቁሙ (ኪዳነ-ወልድ፣ 1948)፡፡
ገ/ክርስቶስ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በተሰኘው የግጥም ምድብልና በጋዜጦች ከወጡት ግጥሞቹ ጋር ተደምረው ከ60 በላይ የሚሆኑ የግጥም ስራዎችን አበርክቷል፡፡ እነዚህ ግጥሞች ከይዘት ትኩረታቸው አንፃር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩሩም ግጥሞቹ የተቃኙት ገብረ-ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ብሎም ስለራሱ ኑባሬ በነበረው የአስተሳሰብ መንፈስ መሆኑ ግጥሞቹ ምስክር ናቸው፡፡ ለዚህ ይመስላል ዮናስ አድማሱ የገ/ክርስቶስን ግጥሞች መሰረት አድርገጎ ገ/ክርስቶስን እንዲህ በማለት የገለፀው፤ “ገ/ክርስቶስ የሚል ተጸውኦ የተሰጠው ሰው፣ ከሰው ይልቅ “ሰውነት” “ሰው መሆን” ኩነኔ የሌለበት፣ ጽድቅ የሌለበት (እንደቅኔው)፣ እሱነቱ እንደወረደ፡፡ በቃ፡፡ የግጥሙ ታህታይ ትርጉም መግጠሙ ነው” (ዮናስ፣ 1998፣ ገጽ 31)፡፡
የሰው ልጅ ኑባሬን መሰረት ባደረገ መልኩ የስነ-ኑባሬ ፍልስፍና በሁለት ተከፍሎ መታየት ይችላል፡፡ እነዚህም መሰረታዊያት ፍልስፍና (essentialist philosophy) እና ነገረ-ህላዌ (existentialism) ናቸው፡፡ መሰረታዊ ፍልስፍና የሚባለው ከጥንታዊ፣ መካከለኛው እና ዘመናዊዩ ፍልስፍናዊ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን በመሰረታዊነት የሰው ልጅን ኑባሬ ከህላዊነቱ አስቀድሞ ረቂቅ ስነ-አዕምሮዊና ስነ-ልቦናዊ በሆኑ መሰረታዊ ባህሪያትና ህግጋቶች (categories) (ማለትም ማሰብ፣ ምክንያት፣ ነፍስ፣ መንፈስ) ሁለታዊ (universal) በሆነ መልኩ ነፍስን (soul) ከአካለ-ስጋ (body) አቃርኖ የመተርጎም ፍልስፍናን ይወክላል፡፡ ከዚህ በተለየ፣ የነገረ-ህላዌ ፍልስፍናን ስንመለከት የሰው ልጅ ኑባሬ ተፈጥሮን ከሰው ልጅ ክስተተ-አካላዊ ህላዌ ተፈጥሮ አንፃር ከራስ ወይም ከግለሰቦች የግል ቅምምስ (self-experience) በመነሳት፣ አካለ-ስጋን ከነፍስ በማወዳጀት መተርጎም ላይ የተመሰረተ ነው Kaufmann, 1956)፡፡
ከላይ በቀረቡት ሁለት የስነ-ኑባሬ የፍልስፍና ዘውጎች አንፃር ገ/ክርስቶስ በግጥሞቹ ስለሰው ልጅ ኑባሬ የሰነዘረውን ሀሳብ ስንመረምር የነገረ-ህላዌ ፍልስፍናዊ አመለካከት እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ ይህ ፅሁፍ ገ/ክርስቶስ (1998) “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በተሰኘው የግጥም ስራው ለሰው ልጅ ኑባሬ መሰረት ሁነው በተለያዩ ግጥሞች የቀረቡ መሰረታዊ ህግጋቶችን (categories) መርምሮ በማውጣት የሰው ልጅ ኑባሬ የተገለፀበትን አግባብ በግጥሞቹ ትስስር በመፍጠር ትርጉም ይሰጣል፡፡ ስለሆም፣ ጥናቱ በሚከተሉት ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፤
የጥናቱ ሥነ-ዘዴ
ግጥም በቃላትና ስንኞች እንደመዋቀሩ መጠን አብዛኛውን ጊዜ ቃላት በግጥም ተቀርፀው በሚቀርቡበት ጊዜ ቃላቱ ከእማሪያዊ ወይም ፍካሬዊ ትርጉሞች አልፈው በመሄድ ተምሳሌታዊና ተረፈ-ሰዋሰው የሆኑ፣ በፊት ለፊት ያልተባሉ፣ በትርጓሜ ብቻ ተፈልፍለው የሚዎጡ ክስተቶችን ይይዛሉ (ዮናስ፣ 1998)፡፡ የኢትዮጵያ የሰም እና ወርቅ ባህል በስነ-ፅሁፍ፣ በተለይም በስነ-ግጥም ላይ ከፍተኛ ቦታ እንዳለው ሁሉ የግጥምን ይዘት ነቅሶ ለማውጣት አንድምታ (Hermeneutics) በግጥሙ የተካተቱ ቃላትና ተምሳሌቶች የያዙትን ሁለትዮሽ (ሰም እና ወርቅ) ትረጉሞች ለመረዳት ያስችላል (Mohammed, 2010)፡፡ በዚህ ጥናትም የሰው ልጅ ነባሬ በምን አግባብ ተገለፀ የሚለውን ለመተንተን እና ትርጉም ለመስጠት በግጥሞቹ ውስጥ ያሉት ቃላትና ስንኞች ካላቸው እማሬዊ እና ፍካሬዊ ትረጉም በላይ በመሄድ ለቃላቶችና ለስንኞች አውዳዊ ትረጉም በግጥሞች ትስስር እና በተዛማች ድርሳናት ንባብ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም፣ አንድምታ (Hermeneutics) የጥናቱ ሥነ-ዘዴ ሆኖ አገልግሏል፡፡
የጥናቱ ትርጉም እና ውጤት
ለሰው ልጅ ህላዌ/ኑባሬ መገለጫ መስረታዊያን ህግጋቶች
ገ/ክርስቶስ በስዕል እና በግጥም ስራው ለቅርፅ በተለይም ለመስመር እና ክብነት፣ ለስፍራ፣ ለንቅናቄ፣ ለእንቅስቃሴ፣ ለአቅጣጫ፣ ለጊዜ፣ ለቦታ፣ ለብርሃን እና ለቀለም ልዩ ትኩረት ይሰጣል (ብርሃኑ፣ 2001፤ ዩናስ፣ 1998)፡፡ ለገ/ክርስቶስ የሰው ልጅ ኑባሬ በነዚህ ከላይ በተገለፁት መሰራታዊ ነገሮች አንድምታ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህ ክፍል እንዴት እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ለገ/ክርስቶስ የሰው ልጅ ኑባሬ ምንነት መገለጫ ሆኑ የሚለውን እንመለከታለን፡፡
ዮናስ አድማሱ እንደጠቆመው፣ በገ/ክርስቶስ አስተሳሰብ የሰው ልጅ ህይዎት በክብነት ይመሰላል፡፡ ክብነት (ክበብ) ሁለንታዊ ትዕምርት (universal symbolic) ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ክብ የውሁድነት እና ፍጽምና (unity and perefection) ምልክት አድርገን እናየዋለን፡፡ ክብነት መነሻው መድረሻውም ስለማይታዎቅ የኅቱምነት (Immaculateness) ትእምርት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል (ዮናስ፣ 1998፣ ገጽ 33)፡፡ ክብነት የዑደት መገለጫ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለገብረ-ክርስቶስ ክብነት ሚስጥር እና ሚስጥራዊነት ይወክላል፡፡ የሰው ልጅ እራስን የመረዳት ፍዳ መልሱ ላይገኝ ይችላል፤ ህላዌ በጊዜ እና በቦታ ሂሳብ ሲመዘን ውስን ባለመሆኑ እራስን ለመረዳት የመጠየቅ ጉዞው ይቀጥላል፡፡ ይህ እራስን የመረዳት ሚስጥራዊነት እንደ ህይዎት ኡደት በክብነት የሚወከል ይሆናል፡፡ ገ/ክርስቶስ ስለክብነት እና ለምን በተለይም በስዕሎቹ ክብነትን እንደሚጠቀም ከህይዎት ሁደት ጋር በማስተሳሰር እንዲህ ሲል ይገልፃል፣
The circle is infinite, unending. It symbolizes the hemisphere and heavenly bodies. it is in line with the search for a solution in life, when it frequently happens that one may believe he has reached the optimum solution only to find, (since art is life itself) that the search must continue, a perfect solution remains forever elusive (Gebre Kiristos quoted in www.blenmagazine.com).
በገ/ክርስቶስ እሳቤ፣ ለህይዎት ፍፁም የሆነ መፍትሄ የለውም፡፡ ለህይዎት መፍትሄ ፍለጋ ስንታትር ዋናውን መፍትሄ ያገኘነው ይመስለናል፤ ሆኖም ግን ፍለጋው አያልቅም፣ ፍፁማዊ መፍትሄ የማይጨበጥ ነውና፡፡ ገ/ክርስቶስ ይህን የህይዎት ክበባዊ ተምሳሌት በስዕሎቹ ላይ ገዝፈው የሚታዩ ሲሆን፣ በክብነት የህይወትን የማያልቅ ጉዞ “መነሻ ለሥዕል” በተሰኘው ግጥሙ የበለጠ እንዲህ በማለት የህይዎትን የማያልቅ ጉዞ በሥዕል ተምሳሌትነት እንዲህ በመቀኘት ይገልፀዋል፤
| አያልቅም ይህ ጉዞ- - - - - - - ማስመሰል መተርጎም በቀለም መዋኘት፤ በመስመር መጫዎት፤ ከብርሃን መጋጨት ለማዎቅ ለመፍጠር ባዶ ቦታ መግባት መፈለግ----- መፈለግ አዲስ ነገር መፍጠር፡፡ ከማይታየውጋር ሄደ መነጋገር፤ ህይዎትን መጠየቅ ሀሳብን መጠየቅ አለምን መጠየቅ |
|
| Gebre Kristos Desta | "Inclining Nude" Oil on hardboard 38" X 35", 1973. |
ግጥሞቹን መሰረት አድርገን በገ/ክርስቶስ ሀሳብ ለሰው ልጅ ኑባሬ መገለጫ መሰረታዊ ህግጋቶችን ስንመረምር ሁለት ሆነው እናገኛቸዋለን፤ ጊዜ እና ስፍራ፡፡ ብርሃን ቀለም ነው፤ ብርሃን ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ቀለም እንደ ብርሃን ጊዜ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ብርሃን ቅንጣቲታዊ ስፍንጥርታ ብቻ ሳይሆን ሞገድም ነው፡፡ የብርሃን ሞገድ አናቶች (wave crests) በመስታዎት መሰል ነገሮች ላይ ሲያርፍ የተለያዩ ቀለማትን ይፈጥራል፡፡ በሰኮንድ ወደ አይናችን የሚደረሰው የብርሃን ሞገድ አናቶች ብዛት የተለያየ ሲሆን የተለያዩ ቀለማትን እናያለን፡፡ ለምሳሌ የብርሃን ሞገድ አናቶች ብዛት ከፍተኛ ሲሆን ሰማያዊ ቀለም ይፈጥራል፤ የሞገድ አናቶች ዝቅተኛ ሲሆን ቀይ ቀለም እናያለን፡፡ ወደ አይናችን የሚገባው የብርሃን ሞገድ በብርሃኑ ምንጭ እንቅስቃሴ ይዎሰናል፡፡ ለምሳሌ ወደ አይናችን የሚገባው የብርሃን ምንጭ ከኛ እየራቀ ከሄደ አይናችን የሚገባው የብርሃን ሞገድ አናቶች እያነሱ ስለሚሄዱ ቀይ ቀለም ስናይ ምንጩ እየቀረበ ሲመጣ በአይናች የምናያቸው የብርሃን ዘንጎች ሰማያዊ ቀለም የበዛባቸው ይሆናሉ (ስንቅነህ፣ 1996፣ ገጽ 95-96)፡፡
በዘመነኛ አንፃራዊነት የሳይንስ ንድፈ-ሀሳብ፣ ጊዜና ስፍራ በብርሃን ፍጥነት እንደመመዘናቸው ጊዜና ስፍራ እንደ ብርሃን ናቸው፡፡ የብርሃን ፍጥነት በጊዜና ቦታ መሳክነት (continuum) ሲመዘን አንፃራዊ ነው፤ ብርሃን በሚጓዝበት አቅጣጫና በሚያርፍበት ቁስ ቅርፅ ለውጥ የሚዎሰን ነውና (Hawking, 1988)፡፡ ቅርፅ (ክብነት፣ መስመር) ስፋራ ናቸው፤ እንቅስቃሴ የጊዜ እና ስፍራ ውጤት ነው፡፡ ለመሆኑ ጊዜ ምንድን ነው? ስፍራስ? የስፍራ ትርጉም በጊዜ ትርጉም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለሆነም ስለ ስፍራ ምንነት ከማየታችን በፊት ስለ ጊዜ ምንነት እንመልከት፡፡
የጊዜ ምንነት
ስለጊዜ ምንነት ገ/ክርስቶስ “ይኸ ጊዜ” በተሰኘው ግጥሙ `ጊዜ ይሄ ይሆን?` በሚል መጠይቅ ሦስት አማራጭ ትርጉሞችን ያቀርባል፤
ምን ይሆን ይህ ጊዜ? |
ከላይ ገ/ክርስቶስ ስለ ጊዜ ምንነት የሰጣቸውን አማራጭ ትርጉሞች በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የጊዜ ትረጉም ሁሉን አቀፍ፣ እልቆቢስ እና ዘላለማዊ ተደርጎ የሚዎሰድበት ትርጉም ሲሆን ይህም ምድረ-ጊዜ (world time) ወይም ማህበረሰባዊ ጊዜ (public time) ይባላል፡፡ ይህ ትርጉም ጊዜ ከተፈጥሮና ከሰው ልጅ ክስተታዊ ለውጥ ጋር በመቀዳጀት በስዓት፣ በቀናት፣ በወራት እና በዘመናት እየተመዘነ ለሰው ልጅ እና ለመዋቅረ-አለም የማይለወጥ እና የማይለጠጥ ተደርጎ የሚወሰድበት አግባብ ነው (Hedegger, 1962)፡፡ ሁለተኛው የጊዜ ትርጉም ከዘመነኛ የአንጻራዊነት ንድፈ-ሀሳብ (relativity theory) መካከል የጊዜ-ህዋ ቡሉኮ (space-time continuum) ከሚገለጽበት ሁኔታ ጋር ይያያዛል፡፡ በአንጻራዊነት ንድፈ-ሀሳብ መሰረት የጊዜ-ህዋ ቡሉኮ የቁስ መከናነቢያ እንጂ በራሱ ሕላዌ የለውም፡፡ በመሆኑም ጊዜ እንደየቁሱ ተለዋዋጭና ተለጣጭ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ለምሳሌ ያክል የሰውን ልጅ እንደቁስ በህዋ ላይ እንዳሉት ትልልቅ አካላት ሲታሰብ ሰው ከብረሃን ፍጥነት በላይ በመሄድ በጊዜ ዠረት ትናትን ዛሬ በማድረግ የጊዜን ምንነት ፍፁም ተቀያያሪ እንዲሆን ያደረገዋል (Hawking, 1988፤ ስንቅነህ፣ 1996)፡፡ ከላይ ከቀረቡት በተለየ ሦስተኛው የጊዜ ትርጉም መሰረቱ ተጨባጭና ተፈጥሮዊ ከሆነው የሰው ልጅ ግላዊ ህላዌ ላይ የሚቀዳ ነው፡፡ በዚህ እስቤ መሰረት ጊዜ ግላዊ እና በእያንዳንዱ ግለሰብ ውልደት እና ሞት መካከል ግለሰቡ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ እያለ የሚከፍለውን ለዋጭ ጊዜ (temporal time) ይወክላል (Hedegger, 1962)፡፡
እንግዲህ ከላይ ስለ ጊዜ የቀረቡ አማራጭ ትርጉሞችን መሰረት አድርገን የገ/ክርስቶስን የጊዜ ትርጉም ስንመለከት በሦስተኛው የትርጉም ዘርፍ የሚያርፍ፣ ከሰው ልጅ ግላዊ ህላዌ ላይ የሚቀዳ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የሰው ልጅ ህላዌ ግላዊ እና በእያንዳንዱ ግለሰብ ውልደት እና ሞት መካከል የተወሰነ ነው፡፡ ጊዜ ግለሰቡ በህልውና ወደ ምድር ከመጣበት በመጨረሻ ግለሰቡ በሞት ይችን አለም ከሚሰናበትበት ሁነት ጋር ተያይዞ ግላዊ እየሆነ የሚያልፍ ወይም ዜሮ የሚሆን ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነው ገ/ክርስቶስ ከላይ የተጠቀሰውን የጊዜ ምንነት መጠይቆች ካቀረበ በኋላ በዚሁ ግጥም መደምደሚያ ላይ ጊዜ በግለሰቦች ሞት ግላዊ እንደሚሆን፣ በመጨረሻም በግለሰቦች ሞት አብሮ እንደሚሞት እንዲህ ሲል የተቀኘ፤
ውሸት ነው ይጠፋል |
ገ/ክርስቶስ ከሰላሳ በላይ በሚሆኑ ግጥሞቹ በተደጋጋሚ እንደገለፀው “ሞት” ለጊዜ ግላዊነት ትርጉም መሰረት ነው፡፡ ጊዜ ግለሰቦች በግላዊ ህላዌ ወደ ምድር ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በሞት ምድርን እስከሚሰናበቱበት ድረስ ያለው የህይዎት ልኬት ወሰን ነው፡፡ ይህ የሰው ልጅ ኡደት በጊዜ አውታር ውስጥ አልፎ የመጨረሻ ሞታችን ሲመጣ ለገ/ክርስቶስ ጊዜ ቀስ ይላል፤ በመጨረሻም ዜሮ ወይም ምንም ሆኖ ከግለሰቦች ጋር አብሮ ያልፍል፡፡ “ሰው ሲሸነፍ” ከተሰኘው ግጥም የሚከተለውን እንመልከት፤
የህይወት ለውጥ ነው ያለ በኑሮ ላይ |
የስፍራ ምንነት
በገ/ክርስቶስ ግጥሞች፣ ለሰው ልጅ ኑባሬ ሁለተኛ መሰረታዊ ህግጋት ሆኖ የቀረበው ሰው በህላዌ ወደ ምድር የሚመጣበት ስፍራ ነው፡፡ የገ/ክርስቶስን የስፍራ ምንነት ከማየታችን በፊት በዘርፉ ጠቢባን ዘንድ ስለ ስፍራ ምንነት የተሰጡ ሦስት መሰረታዊ ትርጎሞችን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው የስፍራ ትረጉም ስፋራን ከፍፁማዊዊ የጂኦሜትሪ እሳቤ ጋር በማያያዝ፣ ስፍራ እልቆቢስ የሆነውን መዋቅረ-አለም የሚያካልል የማይለወጥ ስነ-ምድር ተደርጎ የሚወሰድበት ትርጉም ነው፡፡ የሁለተኛው የስፍራ ትረጉም ከዘመነኛው የአንጻራዊነት ንድፈ-ሀሳብ የጊዜ-ህዋ ቡልኮ እሳቤ ጋር የሚያያዝ ሲሆን ስፍራን እንደጊዜ ሁሉ ፍፁም ተቀያያሪ እና ተለጣጭ እንደሆነ ተደርጎ ከሚዎሰድበት ሀሳብ ጋር ይያያዛል፡፡ ሦስተኛው የጊዜ ትርጉም አንፃራዊ እና የሰው ልጅ በግለሰብ ደረጃ በህላዌ ወደ ምድር ሲመጣ አግባብ ከሚፈጥርበት ማህበረሰብ እና መገለጫዎቹ፣ ተፈጥሮ እንዲሁም ህይዎት ኡደቷን ስትቀጥል የሚገለገልባቸውን ቁሶች እና ሌሎች ነገሮች ጋር የሚያያዝ ህላዌ-ስፍራ (existential spatiality) ነው፡፡ Heidegger (1962) ይህን የስፍራ ትረጉም ሰው በህላዌ ወደ ምድር ተወርወሮ ከመጣበት ምድር የሚቀዳ እንደሆነ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፤
The spatiality of Dasein's encountering the available depends on Dasein's concernful being-in-the-world. To encounter the available in its environmental space remains ontically possible only because Dasein itself is "spatial" with regard to its being-in-the world. . . . Dasein . . . is "in" the world in the sense that it deals with beings encountered within-the-world, and does so concernfully and with familiarity (Heidegger, 1962, p. 138).
ከላይ በቀረቡት የስፍራ ምንነት ትርጉሞች አንፃር ገ/ክርስቶስ ለስፍራ የሚሰጠውን ትርጉም ስንመለከት በሦስተኛው ትርጉም ላይ ያርፍል፡፡ ስፍራ ለገ/ክርስቶስ ሰው በህላዌ ወደ ምድር “ሲመጣ” እራሱን የሚያገኘበት ምድር ነው፡፡ “ያለም መራራነት“ በሚለው ግጥም ገ/ክርስቶስ የሰው ልጅ ህላዌ ወደ ምድር መምጣት፣ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሁነት ማሰብ መመርመሩም ተፈጥሮው እንደሆነ እንዲህ ሲል ተቀኘ
ሰው ሊኖር ባለም ላይ መቸ ተፈጠረ |
ስፍራ ለገ/ክርስቶስ ሁለት አይነት ገፅ አለው፡፡ ሰው ተፈጥሮዊ እና ማህበረሰባዊ እንደመሆኑ፣ ስፍራ ሰው ወደ ምድር ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ለተፈጥሮዊ አካባቢው፣ ለማህበረሰቡ እንዲሁም ማህብረሰቡ በየግለሰቦች ቅምምስ ያበረከታቸው ተመሳስሎቶችን ያካልላል፡፡ ይህ ስፋራ ሰው በግል አኮኻን እንደምርጫው ሲፈልግ አራሱን እያቀረበ ሳይፈልግ እራሱን እያራቀ በጊዜው ሂደት ውስጥ እራሱን የሚያገኝበት ቦታ ነው፡፡ ገ/ክርስቶስ “እንደገና”፣ “አገሬ”፣ “ይራመዳል ገና”፣ “በባዕድ አገር”፣ “እዮሃ”፣ “የጠፈር ባይተዋር” እና “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በተሰኙ ግጥሞቹ ስፍራ ተፈጥሮዊ አካባቢ፣ ማህበረሰብ እና የማሀህበረሰቡ ስርዓቶችን የሚያጠቃልል እንደሆነ እና ግለሰቡ ለእሱነቱ መገለጫ ይሆነኛል ባለ ጊዜ እረሱን እያቀረበ አይሆነኝም ሲል እያራቀ ማንነቱን ለመገንባት የሚያስችለው አቅም እንደሆነ ያመላከተበት ግጥሞቹ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ግጥሞች መካከል በተለይም “በባዕድ አገር” በተሰኘው ግጥሙ አገሩን ለቆ ባዕድ አገር የሄደ ሀበሻ ባዕድ አገሩ እንደ ስፍራ ከእሱነቱ ጋር አልሄድ ሲለው አገሩን የሚናፍቅበት እና የእሱ ማንነት በአገሩ ላይ እንደሆነ የተቀኘበት አግባብ ስፍራ አንፃረዊ እንደሆነና ለእኛነታችን መገለጫ ሳይሆን ሲቀር እራሳችን እንደምናርቅ ያሰገነዝበናል፡፡ ይህ ሃሳብም በሚከተሉት ስንኞች ውስጥ ይንፀባረቃል፤
የርጎ ዝንብ __ የርጎ ዝንብ |
“የጠፈር ባይተዋር” እና “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” የተሰኙ ግጥሞች በተመሳሳይ ገ/ክርስቶስ የሰው ልጅ ስፍራ ግላዊ እና ወሰኑ በግለሰቦች ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ የተቀኘባቸው፣ አንዲሁም በተፈጥሮ እና በማህበረሰብ ጫና ስፍራው ውስን ሲሆንበት በግላዊነት ወሰን አልባ የሆነ ስፍራውን ማሰስ ተፈጥሮውም ፍላጎቱም እንደሆነ የገለፀበት ግጥሞቹ ናቸው፡፡ ለአብነት ያክል የ“መንገድ ስጡኝ ሰፊ” ስንኞች እንዲህ ይነበባሉ፤
ግማሽ ቀልድ አላውቅም! |
ከዚህ በተጨማሪ “እንደገና”፣ “አገሬ”፣ “ይራመዳል ገና” እና “እዮሃ” የተሰኙ ግጥሞች፣ ሰው በህላዌ ወደ ምድር የመጣበት አለም፣ ማህበረሰብ እና የማህበረሰብ ስርዓት ስንመረጠው የእኛነታችን መሰረት እንደሆነ ያመላከተበት ነው፡፡ በተለይም እነዚህ ግጥሞች፣ አንድ ሰው ባዕድ አገር ሆኖ (ምናልባትም ገ/ክርስቶስ ባዕድ አገር በነበረት ወቅት ሊሆን ይችላል) በናፍቆት እና በትዝታ ያጣውን ስፍራ የሚመኝበት ግጥሞች ናቸው፡፡
የሚከተሉትን “እንደገና” ከተሰኘው ግጥም የተወሰዱ ስንኞችን እንመልከት፣
ይናፍቀኝ ነበር - - - - - - - |
ከዚህ በተጨማሪ ስፍራ ግለሰቦች በህላዌነት ምድር ላይ ሲኖሩ በግላዊነት ወይም በጋራ የሚገለገሉባቸው ቁሶችን ይወክላል፡፡ ግለሰቡ ለእነዚህ ቁሶች እራሱን አቅርቦ በተጠቀመባቸው እና ባወቃቸው ቁጥር ግለሰቡ በቁሶቹ መጠቀም እና ማወቅ ውስጥ ህልውና እንዳለው፣ በቁሶችም ውስጥ ኑባሬውን ወይም ማንነቱን እንዲያውቅ ያስችሉታል፡፡ ለስፍራ ገ/ክርስቶስ ከላይ የተሰጠውን አይነት አንድምታ እንዳለው ከሚያመላክቱት ግጥሞቹ መካከል “የሚያፅናኑ” የተሰኘው ግጥም እንመልከት፤
ጅምር ስራ |
ከላይ በቀረበው ግጥም እንደተመለከተው አንድ ግለሰብ ሲኖር ከላይ የተጠቀሱት ቁሶች የሚገለገልባቸው፤ እሱ ጠንቅቆ የሚያውቃቸው፣ ከዚህ ሲያልፍ የግለሰቡ ሀሳብ እና ድርጊት የሚቃኝባቸው ናቸው፡፡ ለገ/ክርስቶስ በህይዎት መንገድ ላይ እነዚህ ሁሉ ቁሶች ለመኖሩማፅናኛዎቹ ናቸው፡፡ መፅናናት በህላዌ ውስጥ ነገን በተስፍ እየጠበቅን በህይዎት ግባችን እንድንጓዝ የሚያደርግ ብርሃን ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ስፍራ እንደቁስ በተገለገልናባቸው እና ባወቅናቸው ቁጥር ህልውና እንዳለን እንድንገነዘብ፤ በዚህም ኑባሬችንን እንድንገነባ አቅም የሚፈጥርልን፡፡
የሰው ልጅ ህላዌ እና ኑባሬ በጊዜና በቦታ መሳክነት
ህላዌ
አለቃ ኪዳነ-ወርቅ ክፍሌ (1948) ስለ ሰው ልጅ ህላዌ ትርጉም ሲሰጡ ሰው በውልደቱ ምክንያት ወደ ምድር ሲመጣ ይዞት የሚመጣው የአካል ህላዌነቱን እንደሆነ ይጠቀስሳሉ፡፡ አካል ማለት “ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ያለው፤ እራሱን የቻለ ለራሱ የበቃ፤ እኔ የሚል ህላዌ፣ ነባቢ ያለው፤ የባህሪ፣ የግብር ባለቤት፤ እገሌ የሚባል” በማለት ይተረጉሙታል፡፡ በአካል ወደ ምድር የመጣ ሰው ከስጋነት ወይም ቁስነት በላይ ለእራሱ የበቃ፤ የባህሪና የግብር ባለቤት ይሆን ዘንድ ህላዌ ያስፈልገዋል፡፡ ህላዌ “መኖር፣ መገኘት፣ መሆን፣ መፈጠር” የሚል ቃላዊ ትርጉም እንዳለው ሁሉ በአካልነት ህላዌ ወደ ምድር የመጣ ሰው አካል ባህሪን ያስከትላል፤ ባህሪ ደግሞ ግብርን ያስከትላል፡፡ ለዚህ ነው አለቃ ኪዳነ ወርቅ ክፍሌ “ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር በአጥንት፣ በጅማት፣ በስጋና በቆርበት ተይዞና ተሸፍኖ ያለው ባድነት አካል መባሉ፣ በነፍስ እውቀትና በነፍስ አካልነት ነው እንጂ በገንዘቡ አይደለም” በማለት ትርጉም የሚሰጡት፡፡ ስለሆነም፤ ሰው በህላዌነት ወደ ምድር ሲመጣ አካለ-ስጋ እና የሚያስብ ህሊና (ነፍስ) ይዞ ይመጣል (ኪዳነ-ወርቅ፣ 1948)፡፡
ለገብረ-ክርስቶስ ሰው ከስጋ (body) እና ከነፍስ (soul) የተገነባ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ አይነጣጠሉም፤ ስጋ ሲኖር ነፍስ ትኖራለች፣ ስጋ ሲሞት ጅማት ሲዝል፣ እስትንፋስ ሲቆረጥ ነፍስ ትጠፋለች፡፡ ነፍስ ሀሳብ ናት፣ መገለጫዋ ስጋ የሚወልደው ሀሳብ እና ድርጊት/ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስለዚህ ስጋ ሲሞት ነፍስም ትሞታለች፣ በስጋ መሞት ሀሳብ ይሞታልና፡፡ ይህን የገ/ክርስቶስ ሀሳብ/እሳቤ ለመረዳት “ማነሽ” ከተሰኘው ግጥሙ ጥቂት ስንኞችን ወስደን እንመልከት፤
እኔ ነኝ የሆንሁት ሳላውቀው አንችን |
በነገረ-ህላዌ ፍልስፍናዊ ምልከታ ለሰው ልጅ ኑባሬ መሰረቱ ህልውነት (existence) ነው፡፡ ሰው በህላዌነት ወደ ምድር ሲመጣ አካለ-ስጋ እና ነፍስ (ህሊና) ይዞ የሚመጣ ሲሁን ህላዌነቱ ለግለሰቡ ቀጣይ ኑባሬ (ማንነቱ) መሰረት ነው፡፡ Heidgger÷ህላዌ እያዳንዱ ሰው በአለም ላይ ተወርውሮ በግላዊነት የመገኘት ተፈጠሮዊ ክስተት (thrown being-there-in-the wold) እንደሆና፣ ሰው በጊዜ ምህዋሩ ውስጥ ለእሱነቱ ገለ-መገለጥ በመፍጠር ኑባሬውን የሚገነዘብበት መሰረቱ ነው በማለት ይገለፃል፤
Man as being-in-the-world is understood in terms of its “existence”. The proposition “man exists” means: man is that being whose Being is distinguished by the open-standing standing-in in the unconcealedness of Being, from Being, in Being. . . . Every project that holds open the truth of Being, representing a way of understanding Being, must look out into time as the horizon of any possible understanding of Being (Heidgger, 1962, p. 32).
ከላይ ስለስፍራ እንደቀረበው፣ ለገብረ-ክርስቶስ የሰው ልጅ ህላዌ ከመሬት ወደ መሬት መምጣት ጋር ይያያዘል፡፡ ሰው ከምድር ወደ ምድር ሲመጣ ልክ እንደተባይ ነው፤ ነፍስ ከሌለው ነፍስ እንደሚፈጠር የተፈጥሮ ሁነት፡፡ ገ/ክርስቶስ “ደብዳቤ” በተሰኘው ግጥሙ እንዲህ ይላል፤
ቆዳ ከጭቅቅት ቅማል አስገኝቶ |
በገ/ክርስቶስ ሀሳብ በህላዌ ሰው ወደ ምድር የሚመጣው ከእያንዳዳችን ሚዛን ውጭ በሆነ ሃይል (Transcendental Power) አይደለም፡፡ ከላይ በቀረበው ግጥም እንደተመለከተው ሰው ከምድር ወደ ምድር የመጣ ነው፡፡ ከዚህ በተለየ በተለየ ሀይል ወደ ምድር መጣሁ የሚል ለገብረ-ክርስቶስ “ሞኘ ተላሌነት” ነው፤ Heidegger (1962) ይህን አይነት ሰው ኑባሬ የሌለው፣ ልዕልና የሌለው ሰው “inauthentic Dasein” ነው በማለት ይገልፀዋል፡፡ ገብረ ክረስቶስ “ሞኘ ተላሌ” በሚል የተቀኘውን እንመልከት፤
ማ መሆኑን ሳያውቅ እራሱን ሳይገምት |
ለገ/ክርስቶስ “በህላዌ” ወደ ምድር መምጣት በመወለድ ይበሰራል፡፡ በመወለድ ውስጥ ሞት አለ፡፡ ከላይ ስለ ጊዜ ምንነት በተሰጠው ትንታኔ ላይ እንደቀረበው ለገ/ክርስቶስ የጊዜ ምንነት ትርጉም በእያንዳንዱ ግሰለሰብ መወለድ እና መሞት መካከል ያለው ወሰን እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ በተለይም ከላይ በቀረበው “ሰው ሲሸነፍ” በተሰኘው ግጥም ውስጥ ተፈጠሮ በተቃርኖ ካቴጎሪ የተሞላች እንደሆነች እና ሰው እንደተፈጥሮ አካል በመወለዱ ውስጥ መሞቱ የወደፊት አይቀሬ እጣው እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ይህንን አይነቱን የገ/ክርስቶስ ሀሳብ Heidegger በዚህ መልክ ይገልፀዋል፤
Factical Dasein exists as born; and, as born, it is already dying, in a sense of being-towards-death. As long as Dasein factically exists, both the ends and their between are, and they are in the only way possible on the basis of Dasein’s being as care . . . as care Dasein is in between (Heidegger, 1962, p. 426-27).
በገ/ክርስቶስ ሀሳብ ይህ በመወለድና በመሞት መካከል ያለው ጊዜ ግለሰቡ ለእሱነቱ እንዲቆም በማስቻል ኑባሬ እንዲኖረው አቅም ይሆነዋል፡፡ ለዚህም ነው “ይኸ ጊዜ” በሚለው ግጥም መደምደሚያ ላይ ሰው በጊዜ ላይ መኖሩን እንደሚያሳይ እንዲህ ሲል የተቀኘው፤
ጨለማ ሲረታ |
ኑባሬ
ህላዌነት በጊዜ እንደመገለፁ እና ህላዌ ለኑባሬ መሰረት እንደመሆኑ የእያንዳንዱ ሰው ኑባሬ ከእያንዳንዱ ግለ-ጊዜ የሚመዘዝ ነው፡፡ እንግዲህ በሞት ምክንያት ጊዜ በግለሰቦች ውስጥ እያለፈ ግላዊ ንብረት በመሆን በልደትና ሞት መካከል ግለሰቡ ትናንት ከአካሄደው እየተማረ፣ ዛሬ እያካሂደው ያለውንና ለወደፊቱ የሚየካሂደውን የህይወት ጉዞ እንዲመዝን ያደርገዋል፡፡ ለገብረ-ክርስቶስ “ሞት ጅምሩ ማለቂያው እንቆቅልሽ” ነው፡፡ በመሆኑ ዛሬን እየኖርን ነገ እንደምንሞት ስናውቅ ለእኛነታችን የምንቆመበትን አቅም ይፈጥራል፡፡ Heidegger (1962) ሞት ለእያንዳንዱ ግለሰብ በምድር ላይ ያለመኖር የመጨረሻ አጋጣሚ ቢሆንም እንደመጨረሻ አጋጣሚ ግለሰቡ ነገ ሟች መሆኑን ሲያውቅ ለእሱነቱ (ለኑባሬው) እራሱ የሚቆምበትን አቅም ይፈጥርለታል በማለት እንደሚከተለው ይገልፃል፤
Death is a possibility-of-Being which Dasein itself has to take over in every case. With death, Dasein stands before itself in its own most potentiality-for-Being. This is a possibility in which the issue is nothing less than Dasein's Being-in-the-world. Its death is the possibility of no-longer being-able-to-be-there (Heidegger, 1962, p. 294).
ለገ/ክርሰቶስ በሞት ውስጥ ህይዎት ይነበባል፡፡ “ለአባቴ” በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ እንደገለፀው የገ/ክርስቶስ አባትየራሱ እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም፣ ልጅ ሞቶበት ሞትን ያውቀዋል፡፡ ሞትን ከማወቅ በተጨማሪ “ህይዎትን ሲያነቡት ወደ ግራ ሞት መሆኑን” ያውቃል፡፡ ህይዎትን ሲያነቡት ወደ ግራ ሞት ከሆነ ሞት ወደ ቀኝ ሲፃፍ ህይዎት ይነበባልና ሞታችንን ባወቅን እና ለሞትም ያለን ፍራቻ በጠፋ ጊዜ ልዕልና (autonomy) ያለን፣ ኑባሬያችንን (Being) ያወቅን እንሆናለን፡፡ የገ/ክርስቶስ አባት ይህን ያውቁ ነበርና፣ በማዎቃቸውም ሞት ሳይቀድማቸው በስራቸውና በምግባራቸው ፍፅምና ህይዎትን ስለዘለቁ በሞት ውስጥ “እረፍት›ት አድርግ አሁን” በማለት ገብረ-ክርስቶስ ሟች አባቱ ትክከክለኛ ሞት እንደሞት ይገልፃል፡፡ እስኪ ገ/ክርስቶስ ስለአባቱ ሞት የተቀኘውን “ለአባቴ” የተሰኘውን ግጥም ጥቂት ስንኞች እንመልከት፤
ሞት እንቆቅልሽ |
ገብረ-ክርስቶስ “ሞኘ ተላሌ” በተሰኘው ግጥም ውስጥ ጊዜ በሞት እንደሚገደብ ያላወቀ ሞኘ ተላሌ “ይኖር የመሰለው አለም እንዲህ ጣፍጣ” እርጅናው ሲመጣ መጨነቁ ሟች መሆኑን አለማዎቁ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ይህ ሰው ለገብረ-ክርስቶስ “ሞኘ ተላሌ” ነው፤ ሞቱን ቢያውቅ ግን ማንነቱን ያውቃል፤
ፍጹም አያስብም ስዓቱ ሲቆጥር |
ሞት ለያንዳነዳችን የነገ አጋጣሚ በመሆን ጊዜን በዛሬ አዬኖርን ትናት እያልን ነጋችንን በድርጊታቸችን የተሻለ ለማድረግ እንድንታትር ደርጋል፡፡ መሞታችንን በጌዜ ሂሳብ መቸ እንደሆነ አለማዎቃችን ደግሞ ከተወለድን ጀምሮ በተስፍ ነገር ግን ሀሳባችንን ስራ፣ ሀሳባችንን ኑሮ፣ ሀሳባችንን ህይዎታችን እያደረግን እንድንኖር ያስችላል፡፡ (ሞት እንደ እንቆቅልሽ ጅምሩ ማለቄው፣ መካከሉ ዳር ነውና) ነገር ግን ሞታችን መቸ ስለመሆኑ አለማወቃችን “ነግን” በማናውቀው መነንገድ ውስጥ በተስፍ እንድንጓዝ፣ ዛሬ ላይ ለኑባሬያችን እንድንቆም አቅም ይፈጥርልናል፡፡ ገ/ክርርስቶስ “ደብዳቤ” በሚለው ግጥም የበለጠ ይህን ይገልጠዋል፤
የሚሰራ የሰው ሀሳቡ ነው |
ሞት ለጊዜ ይህን አይነት ትርጉም ከሰጠ ጊዜ፤ ገ/ክርስቶስ እንዳለው፤ ለመኖራችን ማሳያ መስታዎት እንድንሆን ያደርጋል፡፡ በዚህ የኑሮ መስታዎት የእኛነታችን ገፅ በጊዜ መስታዎት በሀሳብ እና ድርጊት ሲነበብ ማንነታችን/ኑባሬያችን ይሆናል፡፡ለመሆኑ ሰው በጌዜ ላይ ለመኖሩ ማሳያ መስታወት እንዴት ይሆናል? ከላይ እንደቀረበው ጊዜ በሞት አማካኝነት ግለሰባዊ ከሆነ ሞት ደግሞ ለያንዳንዳችን ህሊና ጥንቁቅናን ያላብሰዋል፡፡ ህሊናችን ጥንቁቅ ሲሆን ደግሞ ለእራሱ ለህሊናችን መገለጫ ለሆነው ለየዕለት ሀሳብና ድረጊታችን ሃላፊነትን እንድንውሰድ ያደርገናል፡፡ “ስንኖር” ከሰተኘው ግጥም እነዚህን ስንኞች እንምዘዝ፤
ሁሉም ይለወጣል |
ይህ እንደግለሰብ የምንወስደው ሃላፊነት በራሳችን ሁነት ውስጥ የራሳችንን ማንነት (ኑባሬ) ግለ-ጉዳይ በማድረግ በጊዜ የትናት መሸወለኪነት ግንዛቤን በመወሰድ፤ በአሁኑና በወደፊቱ ድረጊታችን በተወሰነ የራሳችን የግል የህይዎት ግብ “የስሜት ግቡ፣ የልቡ እርምጃ” ውስጥ እራሳችን ለኛነታችን (ኑባሬያችን) የምቆምበት የአቅምና የፅኑነታችን ልኬት ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ የሀላፊነት ልኬት መሰረት ግሰቡ የራሱን ማንነት ግለ-ጉዳይ አድረጎ በራሱ የህይዎት ግብ እና በድረጊቱ የማይገልፅ ከሆነና ጠቅላላ ህልውናውን በሌሎች ሰዎች ወይም ከእሱ ሚዛን ውጭ ባለ አንዳች ሀይል ላይ በመጣል በራሱ ነፃ-ፈቃድ (free will) ማንነቱን ያልገነባ ከሆነ እሱ ለገ/ክርስቶስ “ሞኘ ተላሌ” ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የሰው ልጅ የህይዎት ጉዞ ለህይዎት ግባችን የምናደርገው የህወይት መንገድ፣ ጠመዝማዛም ይሁን ቀጥተኛ፣ ለገብረ-ክርስቶስ የመንገዳችን ብርሃን፣ የህይዎትን ድቅድቅ ጨለማ የሚረታልን ብርሃን ደስታ ነው፡፡ ደስታ በጊዜ የህይዎት ኡደት በምናደርገው የህይዎት ጉዞ የምንፈጥረው፣ የፈጠረርነው እና ለወደፊቱ የምንፈጥረው የህይዎት መብራት ነው፡፡ ይህንንም “ህይዎት” በተሰኘው ግጥሙ እንዲህ ሲል ይቀኝበታል፤
ህይዎት ጨለማ ነው የምንጓዝበት |
ከላይ በተወሰነ መልኩ እንደተገለፀው ገ/ክረስቶስ የስውን ልጅ ኑባሬ የሚገልፀው የሰው ልጅ ህላዌ መሰረት በሆኑት የጊዜ እና የስፍራ ብልኮዎች /መሰረታዊ ህግጋቶች/ ነው፡፡ ጊዜ ከላይ እንደቀረበው መዋቅራዊ፣ ዘላለማዊ እና ማህበራዊ ሳይሆን ግለሰባዊ እና በሰው ልጅ ሞት እና ልደት የሚመዘን ነው፡፡ በዚሀ የሰው ልጅ ህላዌነት ሰው እራሱን በሀሳቡ እና በድርጊቱ በራሱ የህይወት ግብ ወይም የልቡ እርምጃ ሲጓዝ ከጊዜ በሻገር አግባብ የሚፈጠርበት ምድር (ስፍራ) መኖሩ ተፈጥሮው ነው፡፡ ከገብረ-ክርስቶስ “የጠፈር ባይተዋር” የተሰኘ ግጥም የሚከተሉትን ስንኞች እንመልከት፣
የመሬት ቁራጭ ነኝ |
ሰው የመሬት ቁራጭ ከሆነ መሬት የተወለድንበትን አካባቢ፣ ተፈጠሮ፣ ማህበረሰቡ እንዲሁም ማህበረሰቡ የሚገለፅበት ባህል በባህል ውስጥ የሚካተቱ ማለትም ቋንቋ፣ ሀይማኖት፣ ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት፣ የጋብቻ ስርዓት፣ ኪነ-ጥበብ፣ ሳይንስ፣ ወ.ዘ.ተ. ነገሮች ሰው በህላዌ ወደ ምድር ሲመጣ አግባብ የሚፈጥርባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ከላይ እንደቀረበው ለገ/ክርስቶስ ይህ ስፍራ ሁለንታዊ ሳይሆን ግለሰባዊ ነው፡፡ በዚህ አግባብ በግለሰቡ ግለ-ጊዜ ውስጥ ግለሰቡ ለዚህ ስፍራ እራሱን ሲያቀርብ እና ሲያርቅ ማንነቱን ይገነባል ማለት ነው፡፡
ኑባሬ ግላዊ ሲሆን ግለሰቦች በግል ጊዜና ቦታ መሳክነት ቅይይራዊ በሆነ መልኩ በሀሳቡ እና በድርገቱ የሚገነቡት ማንነት ነው፡፡ ከጊዜ አንጻር የልዕለ-ሰቡ ሁነት በትናንት፣ ባሁን እና በነገው የጊዜ ጉዞ ዉስጥ መሆንን ሲያመለክት ግለሰባዊነቱ በያንዳንዱ ግለሰብ ዉልደት እና ሞት መካከል በተወሰነ የግለሰቡ የህይዎት ግብ ግለሰቡ ያካሄደውን፣ እያካሄደ ያለውን እና ለወደፊቱ የሚካሂደውን የሀሳቡ ውጤት የሆነውን የድርጊት እና የለውጥ ፍትጊያ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ጊዜ በትናት እንደ ታሪክ እየተበየነ ለአሁኑና ለነገ የግሰቡ ኑባሬ ምንጭ ለሆነው ድርጊቱ ሚዛን በመሆን ተቀያያሪ ማንነቱን ከህይዎቱ ግብ አንፃር እዲገነባ ያስችለዋል ማለት ነው፡፡ ስፍራ ከላይ እንደቀረበው ግለሰቡ በውልደቱ ምክንያት ወደምድር ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሊገኝበት የሚችለውን ተፈጥሮዊ የሆነውን አካባቢውን፣ ማህበረሰቡንና የማህበረሰቡ መገለጫ የሆነውን ባህል፣ ሀሪሶት (culture)፣ ደንብ፣ ልምድ፣ ባህሪ፣ ሀይማኖት፣ ማህበረሰቡ በግለ-ጊዜ ድምር ያበለፀገው ታሪክ እና እነዚህ በግለሰቦች የግል እና የጋራ ብዛ-ተግባቦት የተመሰረቱ ተመሳስሎቶች በጊዜ ሂደት የሚተላለፉበትን ቋንቋ ያመላክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስፍራ ግለሰቡ በህይዎት ውስጥ እራሱን አቅርቦ የሚገለገልባቸውን እና የሚያውቃቸውን ቁሶች ይጨምረል፡፡ እንግዲህ ይህ ስፍራ በግለሰቡ የጊዜ መሳክነት ውስጥ በእሱ ነፃ-ፈቃድ ሲመረጥ የኑባሬ መገምቢያ አቅም ይሆናል ማለት ነው፡፡
ማጠቃለያ
ከላይ በዝርዝር እንደቀረበው በገ/ክርስቶስ ሀሳብ ለሰው ልጅ ኑባሬ መሰረቱ ህላዌ ነው፡፡ ይህ ህላዌ ከምድር ወደ ምድር መምጣት ሲሆን በአንድ በተወሰነ የጊዜ እና ስፈራ መሳክነት ውስጥ መከሰት ነው፡፡ እንደ ገ/ክርስቶስ ሀሳብ÷ የሰው ልጅ ህላዌ በመወለድ የሚበሰር ሲሆን በመሞት ይጠናቀቃል፡፡ ሰው በህላዌ ወደ ምድር ሲመጣ አካለ-ስጋ እና የሚያስብ ህሊና ይዞ የሚመጣ ይመጣል፡፡ በጊዜ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በነገው ሞቱ አይቀሬነት ጥንቁቅናን በመላበስ ከትናት በመማር ዛሬ ላይ ሀሳቡን ድርጊት፣ ሀሳቡን ስራ እያደረገ ነገን በዛሬ ላይ ሲኖር ኑባሬውን በኑሮው ይገነባል፡፡ የሰው ልጅ የእራስ ኑባሬ ግለ-መገለጥ (disclosure to one’s Being) ገቢራዊነት በቅይይረዊ ጊዜ እና ህላዌ-ስፍራ መሳክነት በግለሰቡ ሀሳቡ እና ድርጊቱ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ዋቢዎች
ሀ. የአማርኛ ዋቢዎች
| ስንቅነህ እሸቱ (1996)፡፡ 40 ጠባታዎች:: አዲስ አበባ:: |
| ብርሃኑ ድንቄ (1987)፡፡ አልቦ ዘመድ፡፡ የታተመበት ያልተገለፀ፡፡ |
| ብርሃኑ ገበየሁ (2001)፡፡ “ዘመናዊ የአማርኛ ግጥሞች አንዳንድ ነጥቦች”፣ በመድበለ ጉባኤ (አርታኢ ደረጃ ገብሬ)፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፡፡ |
| ዩናስ አድማሱ (1998)፡፡ “ያላለቀመግቢያ” በመንገድ ስጡኝ ሰፊ (ገብረ ክርስቶስ ደስታ) ፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም፣ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ፡፡ |
| እጓለ ገ/ዮሃንስ (1958)፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፡፡ የታተመበት ያልተገለፀ፡፡ |
| ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (1948)፡፡ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ አዲስ አበባ፡ |
| ገብረክርስቶስደስታ (1998)፡፡ መንገድ ስጡኝሰፊ፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም፣ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ፡፡ |
| ፀጋዬ ገ/መድን (1986)፡፡ እሳት ወይ አበባ፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፡፡ |
| ፈቃደ አዘዘ (2001)፡፡ በጀርመን ባህል ማዕከል ለገ/ክርስቶስ ደስታ መታስቢያ ገ/ክርስቶስ |
| ገጣሚ ወይስ ስዓሊ በሚል በቀረበው ወይይት ለውይይቱ መክፈቻ ንግግር የተወሰደ፡፡ |
ለ. የእንግሊዝኛ ዋቢዎች
| Blen GraFix & Artworks. “Honoring the Painter Poet Gebre Kristos Desta” www.blenmagazine.com |
| Hawking, S. (1988). The Brief History of Time. Bentam Dell Publishing Group. |
| Heidegger, M. (1962). Being and Time. Oxford: Blackwell. |
| Kaufamann, W. (1956). Introduction . In W. Kaufamann, Existentialism: From Dostovsky to Sartre (pp. 11-51). New York: Meridian Books, INC. |
| Levi-Strauss, C. (2001). Myth and Meaning, The 1977 Massey Lectures. Routledge. |
| Mohammed, G. (2011). Whose Meaning'? The Wax and Gold Tradition as a Philosophical Tradition for an Ethiopian Hermeneutic. SOPHIA , 50:175-189. |