የመጽሐፍ ግምገማ

መስከረም ለቺሳ፣ (ኢ)ዩቶፕያ፣ ለእንግሊዝ መንግስታዊና ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ምክንያት የኾነው የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ሥርዓተ- መንግሥትና የሕዝቧ አኗኗር፤ እውነተኛ “ኅዳሴ” ወይም “ተሃድሶ” ከምንታዌነት (Dualism) ወደተዋሕዶ (Unity) የሚደረግ ኹሉን አቀፍ ኅብረተሰባዊ የንስሓ ጉዞ መኾኑን የሚያሳይ ተጨባጭ እና ታሪካዊ ማስረጃ፤ የትርጉም ሥራና የምርምር ማስታወሻዎች፡፡ 2006 ዓ.ም. (2014 G.C.)፣ የገጽ ብዛት 348፣ ዋጋ 85 ብር (35 ዶላር)

ጥላሁን በጅቷል ዘለለው1

መግቢያ

ይህ መጽሐፍ በይዘቱ ረገድ አዲስና ያልተለመደ “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” የሚል ሙግት ያቀርባል፡፡ የመጽሐፉ አቀራረብ እ.ኤ.አ. በ1516 የታተመውንና የእንግሊዛዊው የቶማስ ሞር ስራ የሆነውን ዩቶፕያን ወደ አማርኛ በመመለስ ከትርጉም ባሻገር የደራሲዋን/ተርጓሚዋን የምርምር ማስታወሻዎች አካትቶ ከላይ የተጠቀሰውን ሙግት በማስረጃ ለመደገፍ ሙከራ የሚያደርግ ስራ ነው። ከተለመደው የቃሉ ትርጓሜ በተለየ ተርጓሚዋ/ደራሲዋ ቶማስ ሞር ዩቶፕያን የጻፈው ስለ ኢትዮጵያውያን አኗኗር በቀደሙት ክፍለ ዘመናት በአውሮጳውያን ዘንድ ሲናፈስ በነበረው ዜና እንዲሁም በፖርቱጋላውያን አሳሾች የጉዞ መጣጥፎች ላይ ተመስርቶ ሊሆን እንደሚችልና ከቶም ልቦለዳዊ እንዳልሆነ በመሞገት “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ”፣ በቶማስ ሞር መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰችው ገነት መሳይዋ ስፍራም ጦቢያ፣ ሕዝቦቹም ኢትዮጵያውያን ናቸው ትላለች፡፡ የቶማስ ሞር ዩቶፕያ በወጥ ትርጉም መልክ (በአማርኛ) ሲቀርብ በአገራችን ይህ የመስከረም ስራ የመጀመሪያው ይመስለኛል። ተርጓሚዋ/ደራሲዋ ከትርጉም ስራዋ ባሻገር ያነሳችው ጉዳይ ፍልስፍናዊ ወይም ርዕዮተ-ዓለማዊ ነው። ስለ “ምንታዌነት”ና ስለ “ተዋሕዶ” ጽነሰ-ሀሳቦች አስመልክቶ በሰፊው የሞገተች ሲሆን የምዕራባውያን አመለካከት “ምንታዌ” (dualist) እንደሆነና የኢትዮጵያውያን ደግሞ “ተዋሕዷዊ” (unionist) በመሆኑ ወደዚህ “ተዋሕዷዊ” አመለካከትና አኗኗር ስንመለስ ብቻ የድሮዋን ኢትዮጵያ “ዩቶፕያ/ጦቢያ” ልናገኛት እንደምንችል በግርጌ ማስታወሻዎቿና “የምርምር ማስታወሻዎች” ባለቻቸው ጽሁፎቿ ታጠይቃለች።

1 ጥላሁን በጅቷል ዘለለው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሂዩማኒቲስ ፋክልቲ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል፣ ረዳት ፕሮፌሰር ነው፡፡ ኢሜል፣ tilahunbz@yahoo.com

መስከረም እነዚህን ሁለት ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሀሳቦች ከተነሳችበት ዋና ጉዳይ ማለትም ከዩቶፕያና ከ“ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” መሰረታዊ ሙግት ጋር አያይዛዋለች። በትንታኔዎቿም ቄሱ ንጉስ (Prester John) ራሱ የተዋሕዶ አምሳል መሆኑ ተወስቷል። ይኸውም ቄስ ሲሉ ንጉስ፣ ንጉስ ሲሉ ቄስ የሆነ፣ ሁለቱ ማንነቶች (እንበለ ተፈልጦ) የተዋሐዱበት፣ ክህነትና መንግስት በተዋሕዶ አንድ የሆኑበትን የፕሪስተር ጆንን/የቄሱን ንጉስ አርዓያነት ታነሳለች። ይህንንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ባህሪ ጋር በማሰናሰል አምላክ ሰው፣ ሰው አምላክ የሆነበትን ተዋሕዷዊ አስተምሕሮ ለሰው ልጆች አኗኗር መሰረት ሊሆን እንደሚችል/እንዳለበት በመጠቆም፣ አንድ ሰው/አንድ ክርስቲያን መንፈሳዊና ዓለማዊ የሚባል ተፈልጦ/ሁለት ማንነት ሊኖረው እንደማይገባ፣ ይልቁንም የክርስቶስን ተዋሕህዶ ሊወርስ እንደሚገባ ጽፋለች።

ይሁንና ከሥርዓተ መንግስት አንጻር ያነሳችው የቄሱ ንጉስ ዓይነት የመንግስት ስርዓት በኢትዮጵያ ብቻ የነበረ ሳይሆን በበርካታ አገራት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ቲዮክራሲ (theocracy) በመባል የሚታወቅ ነው። ይህም ማለት ቄሶች/ካህናት በእግዚአብሔር ስም ሕዝብን የሚያስተዳድሩበት ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት (በተለምዶ ከክርስትና አንጻር the union of church and state ተብሎ ቢታወቅም) ቤተ- እምነትና ቤተ-መንግስትን አጣምሮ የያዘው የአስተዳደር ሞዴል ዛሬም ድረስ ክርስቲያን ባልሆኑ አገራትም ጭምር ይስተዋላል። (ለምሳሌ ዛሬ በሙስሊም አገራት ያለውን የሸሪአ ሥርዓትና እስላማዊ መንግስትን ልብ ይሏል።) በመስከረም መጽሐፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ተሐድሶ ወይም ሕዳሴ መፍትሄ ተብሎ የቀረበው ወደ ቄሱ-ንጉስ ጦቢያ መመለስ እንደምን በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እውን ሊሆን እንደሚችል መልሱ ግልጽ አይደለም። እናም በሽፋን ገጹ ላይ የተጠቀሰው “ኹሉን አቀፍ የንስሓ ጉዞ”፣ “ማንን ይዞ? እነማንንስ ትቶ?” የሚል ጥያቄ ስለሚያጭር፣ የጸሐፊዋን “ኹሉን አቀፍ” ጥሪ በእውኑ ኹሉን-አቀፍነት አጠያያቂ ያደርገዋል። (በዚህ ዙሪያ ወደኋላ በመደምደሚያዬ እመለስበታለሁ።)

እንግዲህ መስከረም ለአውሮጳውያን ዘመነ-አብርሆት (Enlightenment) አነቃቂ ብቻ ሳይሆን ምክንያት ሆኗል የምትለው የኢትዮጵያው የቄሱ ንጉስ መንግስት ዛሬ ላለችው ኢትዮጵያ እንዴትና ምን ሊፈይድ እንደሚችል የፖለቲካ ምሁራን የተሻለ መልስ ሊሰጡበት የሚችሉ ሲሆን ስለተዋሕዶ ሁሉን-አቀፍ የአኗኗር መንገድ አዋጭ ስለመሆን አያይዛ ያነሳችው ዐቢይ ሙግት ግን በርካታ የዜግነት (citeznship)፣ የአገር ግንባታ/ምስረታ (nation building)፣ የሥርዓተ-መንግስት (government)፣ ተያይዞም የብዙኅነት አስተዳደር (diversity management) ጥያቄዎችን የሚያጭር ነው። ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ክፍሎች፣ በመጽሐፉ ይዘት ላይ ትኩረቴን የሳቡ አንዳንድ ነጥቦች ላይ ምልከታዬን አካፍላለሁ፡፡ በመጨረሻም፣ መጽሐፉ ከ348 ገጾች ባሻገር ምን እንደሚያስተላልፍ፣ ግላዊ ንባቤ ላይ የተመሰረተ አስተያየት በመስጠት መጣጥፌን እቋጨዋለሁ፡፡

I

በቅድሚያ የዚህ ስራ ወደ አማርኛ መመለሱ ተርጓሚዋን በእጅጉ የሚያስመሰግናት ጉዳይ ነው። በተለይ፣ በተለይ አገራችንም ሆነች ዓለማችን ባለችበት የመንፈሳዊነትና የስነምግባር ንቅዘት ወቅት ስለ ስነ-መንግስት፣ ባህልና ስነ-ብዕል/ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ለየት ባለና ለራሳችን እንግዳ በሚመስል ፍልስፍናዊ (ተዋሕዷዊ) እይታ እንድንመለከተው ማድረጓ መልካም ነው። ምናልባት ራሷ ደራሲዋ/ተርጓሚዋ እንደሰጋችው በ“ምንታዌ” አስተሳሰብ ውስጥ ላሉ አንባቢያን ሊዋጥላቸው ባይችልም፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ ፍልስፍና እንዲፈጠር ምናልባትም እንዲመለስ ለማድረግ መሞገትዋ ከመጽሐፉ የምናገኘው ትሩፋት ነው:: በመስከረም “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” በሚለው ድምዳሜ የሚገረም አንባቢ ቢያንስ ሰናይ፣ ገነታዊና ከዚህ- ዓለም-ያልሆነ መሳይዋ ዩቶፕያ የጥንትዋ ኢትዮጵያ ሆነችም አልሆነችም ቶማስ ሞር ዩቶፕያን እንዲጽፍ ያነሳሳው ማህበራዊና ስነ-መንግስታዊ ቀውስ ግን የዛሬዋን አገራችንን (ምናልባትም ዓለማችንን ጭምር) ቀፍድዶ የያዛት ችግር መሆኑ ይህ የትርጉም ስራ ዛሬ የቆምንበትን እንድናስተውል ይጋብዘናል (If Utopia in the affirmative is not what Ethiopia was, its negative surely is what Ethiopia is today!):: በሌላ አነጋገር በቶማስ ሞር ዩቶፕያ ውስጥ የተጠቀሱ ወይም የተነቀሱ ማህበራዊ ጉድፎች የዛሬ ችግሮቻችንን ለመግለጽ ያንሱ እንደሆን እንጂ አይበዙም ለማለት ይቻላል። በመሆኑም የተርጓሚዋ ስራ ከምርምር ማስታወሻዎቿ ባሻገር ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ተርጓሚዋ እጅግ ቀላልና ግልጽ በሆነ ቋንቋ የትርጉም ስራውን ማቅረቧ ሌላው ጠንካራ ጎን ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አቻ አማርኛ ቃላት ያላቸው የማይመስሉ ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሀሳቦችን በቀላልና ባልተወሳሰበ መልኩ ማቅረቧ ወደፊትም በምዕራባውያን ቋንቋ የሚገኙ ዘመን አይሽሬ (classics) ስራዎችን ወደ አማርኛ በመመለስ እንደምታስነብበን ተስፋ ማድረግ ይቻላል።

ሌላው ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ወጥ የሆነ የጸሐፊነት/የደራሲነት ማንነት አሳይታለች። አንድ ጸሐፊ ወይም ተመራማሪ ሚዛናዊ መሆን አለበት በሚል ስም ሁለት ማንነት እንዲኖረው ይገደዳል። በምሳሌ ለመደገፍ ያክል፣ ዓለማዊ ጉዳይ ላይ የሚጽፍ ተመራማሪ፣ ሃይማኖታዊ ማንነቱ እንዳይቀላቀልበት ወይም ስራውን እንዳይበርዝበት ለመጠንቀቅ እንደሚሞክረው ማለት ነው። ይሁንና በመስከረም አጻጻፍ ውስጥ ይህንን መፈለግ መድከም ነው የሚሆነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ምንታዌ ማንነት በተለይም ሃይማኖታዊና ዓለማዊ የተባለ ሊኖረው እንደማይገባ የፕሪስተር ጆንን (የቄሱን ንጉስ) ማንነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ባህሪ ጋር በማነጻጻር በሰፊው መሞገት ብቻ ሳይሆን ራስዋ ጸሐፊዋም የተሟገተችለትን በጽሁፏ ውስጥ ኖራዋለች ለማለት ይቻላል። ስለዚህ የሃይማኖት ወገንተኝነት አለባት የሚል አንባቢ ቢኖር፣ መልሱ፤ “ደራሲዋ በዚህ ልትከሰስ አይገባትም” ይሆናል። ለምን ቢሉ እየተሟገተችለት ያለውን “ተዋህዷዊ” ማንነት በጽሑፎቿ እየተገበረችው ስለሆነ። በመሆኑም በጽሑፍም ሆነ በምርምር ስራ ውስጥ ገለልተኝነትን የሚጠብቅ አንባቢ በመስከረም ስራ ውስጥ ያንን ፍለጋ መባዘን የለበትም። ምክንያቱም ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ሃይማኖታዊ አድሏዊነት ሳይሆን፣ ግልጽ የሆነ ሃይማኖታዊ ትጋቷን የምታንጸባርቅበት ጽሑፍ ነው ማለት ይቻላል።

II

በቅደሚያ የቶማስ ሞርን ዩቶፕያ በተመለከተ ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ሁለት ዐቢይ ሙግቶችን አስቀምጣለች ማለት ይቻላል። እነሱም “ዩቶፕያ ልብወለድ አይደለም” እና “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” የሚሉ። ለነዚህ ነጥቦች ማስረጃ ያለቻቸውን በዝርዝር ያቀረበች ሲሆን፣ ትኩረቴን የሳቡ ጉዳዮች ላይ ጥቂት አስተያየቶችን እሰነዝራለሁ።

“ኢልቦለዳዊቷ” ዩቶፕያና ኢትዮጵያ

መስከረም ይህንን የቶማስ ሞር ስራ በአትኩሮት እንድትይዘው ብሎም ከመተርጎም አልፎ “ዩቶፕያ” ልቦለድ አይደለም፤ ይልቁንም “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” እንድትል ያደረጓትን ምክንያቶች አስቀምጣለች። ከነዚህም መካከል የንቡረ-እድ ኤርምያስ ከበደ መጻሕፍት እና ከርሳቸው ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ስለመሆኑ ትጠቅሳለች። በተለይ ከንቡረ-እድ ኤርምያስ ከበደ ጋር በተደረገ ውይይት የቀሰመችውን እንዲህ ትገልጸዋለች።

‘ዩቶፕያ’ የሚለው ቃል መልካም አኗኗርን የሚገልጽ እንደኾነ፥ መልካም ነገር ደግሞ አንዲት እንደኾነችና ያችውም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደኾነች በመግለጽ ‘ዩቶፕያ’ የሚለው ቃል ኢትዮጵያን የሚገልጽ ከመኾን በቀር ሌላ ሊኾን እንደማይችል አብራሩልኝ። በዚህ ማብራሪያ ረክቼ በዚያ ስም የተጻፈ መጽሐፍ ማግኘቴንና እርሳቸው ያውቁት እንደኾነ ስጠይቃቸው ‘ዩቶፕያ’ ከሚለው ቃል በቀር በዚያ ስም የተጻፈ መጽሐፍ ስለመኖሩም ጨርሶ እንደማያውቁ ገለጹልኝ። ((ኢ)ዩቶፕያ፣ ገጽ 221)

ትለንና በነገሩም ተገርማ ስለመጽሐፉ የበለጠ ማስረጃ ለማግኘት መሞከሯን አስቀምጣለች። ከዚህ ቀደም (ገጽ 220) ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ድርሰቱ ልቦለድ እንዳልሆነ ብታምንም መጽሐፉ የሚተረክላቸው ሕዝቦች ግን ክርስቲያኖች ሳይሆኑ “የባዕድ አምልኮ ተከታይ እንደኾኑ ተደርጎ” በመተረኩ በእርግጠኝነት “ድርሰቱ ስለኢትዮጵያውያን የተጻፈ ነው” ለማለት እንዳልቻለች ገልጻለች። ይህን አመለካከቷን ያስቀየራት ግን ከላይ እንደተጠቀሰው የንቡረ-እድ መጻሕፍትና ከርሳቸው ጋር የተደረገ ውይይት እንጂ የራሱ የመጽሐፉ ይዘት እንዳልሆነ ለአንባቢ ፍንጭ ይሰጣል። ይህ ሁኔታ ደግሞ በቶማስ ሞር መጽሐፍ ውስጥ ታሪክ በዘገበውም ሆነ በአፈታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያውያን ልማድ፣ ጠባይ፣ ባህል ወዘተ. ያልሆኑ ወይም የጥንቷንም ሆነ የዛሬዋን ኢትዮጵያ የማይገልጹ በርካታ ነጥቦችን ወደጎን በማለት ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ለተነሳችበት “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” ለሚለው ትርክት ብቻ ተስማሚ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ግቧን ለማሳካት የሞከረች ያስመስላታል። መስከረም በቶማስ ሞር ስራ ውስጥ በተለይ ኢትዮጵያን የማይመስሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሟት በግድ ጠምዝዛ ለማገናኘት የምትሞክር ይመስላል። ለምሳሌ ስለጥንቷ ኢትዮጵያ የማይመስል ግን ስለዛሬዋ የሚመስል ጉዳይ ሲያጋጥማት “ቶማስ ሞር እየተነበየ ሲነግረን መሆኑን እንገነዘባለን” ወዘተ. (ገጽ 321ን እንዲሁም በተለይ ገጽ 83ን ስለአፍሪካ በአምሳ አራት ከተሞች መከፋፈል ትንቢት ተመልከት) በማለት የምትሰጣቸውን አስተያየቶች ለመቀበል እጅግ ከባድ ይሆናል።

ከላይ እንደተጠቀሰው ተርጓሚዋ/ደራሲዋ መጽሐፉ ስለኢትዮጵያዊያን አይደለም ለማለት ያበቃት ስለባዕድ አምልኮ ተከታዮች እንጂ ስለ ክርስቲያኖች ባለማውራቱ እንደሆነ ልብ እንላለን። ምንም እንኳን የትኛዋ ኢትዮጵያ በጠቅላላዋ ፍጹም ክርስቲያን ሆና እንደኖረች ባናውቅም ቅሉ የቶማስ ሞር ስራ ስለባዕድ አምልኮ ተከታዮች ማውራቱ ደራሲዋን/ተርጓሚዋን ስለኢትዮጵያዊያን የተጻፈ አይደለም ለማለት አነሳስቷት እንደነበረ ሁሉ (ገጽ 220) በድርሰቱ ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን “ለማይመስሉት” በርካታ ነጥቦችና ጉዳዮች (ገጽ 155፣ 194፣ 198፣ 200፣ 203) ዋጋ ለሰጠ አንባቢ ደግሞ የቶማስ ሞር ስራ ልቦለድ ሆነም አልሆነም “ዩቶፕያ” ስለኢትዮጵያውያን አይደለም ለማለትም ይችላል፤ አለያም ቢያንስ ወጥ ያልሆነ ንጽጽር ውስጥ ገብቶ “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ” ነች የሚል ድምዳሜ ላይ ከመድረስ ይታቀባል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዩቶፕያ ስለኢትዮጵያ መሆን ከቻለ፣ ስለህንድ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም ብሎም መሞገት ይቻላል። ለምን ቢባል፣ ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ኢትዮጵያን ስለማይገልጹ ችላ ያለቻቸው ጉዳዮች፣ ለአብነት ያህል ሬሳ ማቃጠልና ስለ“ባዕድ አምልኮ” ተከታዮች ማውራቱ ወዘተ. “ዩቶፕያ ስለህንድ ነው የሚያወራው” ብሎ መላ ምት ለማስቀመጥስ ስለምን አይቻልም? እንደውም የፕሪስተር ጆን (የቄሱ ንጉስ) ሀገር ትሆን እንደሆን በአውሮጳውያን ዘንድ ግምት ይሰጣቸው ከነበሩ ሀገራት መካከል ደራሲዋም ጠቆም እንዳደረገችው (ገጽ 225) ህንድ አንዷ እንደነበረች ልብ ይሏል።

ደራሲዋ/ተርጓሚዋ የቶማስ ሞር ድርሰት ልቦለድ ላለመሆኑ ፍንጭ ይሰጣሉ ካለቻችው ነጥቦች መካከል ሌላው የገጸ-ባሕሪ አሳሳል ጉዳይ ነው። መስከረም እንዲህ ትላለች፤

ቶማስ ሞር ይኽን ጽሑፍ የጻፈው በልብ-ወለድ መልክ ከኾነ መጀመርያውኑ ‘ራፋኤል ሂትሎዴይ’ የሚባል ኹሉንም ነገር እርሱው የሚተርክ ገጸ-ባሕሪ መፍጠር ለምን አስፈለገው?” የሚለው ጥያቄ ማንም አንባቢ ሊያነሳው የሚችለው ግልጽ ጥያቄ ነው። ራሱ ቶማስ ሞር በአንደኛ መደብ “እኔ ተጓዝኩ፥ እኔ ዞርኩ፥ አየሁ” እያለ መጻፍ ሲችል የአንደኛውንም ኾነ የሁለተኛውን መጽሐፍ ትረካ “ሙሉ ለሙሉ” ማለት በሚያስችል ኹኔታ ለሌላ ሦስተኛ መደብ ገጸ-ባሕርይ መስጠቱ ከተለመደው የልብ-ወለድ ጽሑፍ አቀራረብ ጋር አብሮ የሚኼድ አይደለም። ((ኢ)ዩቶፕያ፣ ገጽ 222-23)

ይህ ክፍል የትየባ ስሕተት እስኪመስለኝ ብዥታን ከፈጠሩብኝ የመጽሐፉ ክፍሎች አንዱ ነው። ደራሲዋ “ማንም ሊያነሳው የሚችለው ጥያቄ” ላለችው መልሱ “ልብ-ወለድ ስለሆነ ነው” ነው — ልቦለድ ገጸ-
ባሕሪ ስለሚያስፈልገው። እንደውም ቶማስ ሞር “እኔ ተጓዝኩ፤ ዞርኩ፤ አየሁ” እያለ ሊጽፍ ይችል የነበረው ምናልባትም መስከረም እንዳለችው ዩቶፕያ ኢልቦልድ ቢሆን ኖሮ ነበር። ስለዚህ ታሪኩ በአንደኛ መደብ ትረካ “እኔ አየሁ” ወዘተ. ተብሎ አለመቅረቡ እንደውም የልቦለዳዊ እንጂ የኢልቦለዳዊ ጽሑፍ ባህሪ ሊያደርገው አይችልም። “እኔ” ብሎ በአንደኛ መደብ ጽፎት ቢሆን ኖሮ ተኣማኒነትን የሚጨምር ስለሚሆን ልቦለድነቱን ሳይሆን ይልቁንም ኢልቦለዳዊነቱን ነበር ሊያሳይ የሚችለው። ከዚህ ባሻገር አንድ ደራሲ የትረካውን አንፃር በአንደኛም ሆነ በሦስተኛ መደብ ሊገነባ ይችላል። ስለዚህም ራፋኤል ሂትሎዴይ ሦስተኛ መደብ ተራኪ ይምሰል እንጂ በአንደኛ መደብ “እኔ” እያለ የሚተርክ በመሆኑ የዩቶፕያ የትረካ አንፃር አንደኛ መደብ ነው ማለት ይቻላል። እናም “ቶማስ ሞር ለምን ገጸ-ባሕሪ መፍጠር ፈለገ?” ለሚለው መስከረም ላነሳችው ጥያቄ መልሱ “ዩቶፕያ ልቦለድ ስለሆነ ነው” ማለት ይቻላል።

ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ያነሳችው በመካከለኛው አውሮጳ ምናባዊ መቼትና ገጸ-ባህሪያትን ፈጥሮ መጻፍ የተለመደ አለመሆኑንና ልቦለድ መጻፍ ውሸት እንደመናገር የሚቆጠር በመሆኑ (ገጽ 223) የቶማስ ሞር ስራ ልቦለዳዊ አይደለም ለማለት እንደሚያስችል ትገልጻለች። ይሁንና በአውሮጳ የመካከለኛው ዘመን የስነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ፣ የቶማስ ሞር ዩቶፕያ በ1516 ከመታተሙ እጅግ ቀደም ብሎ ምናባዊ ስራዎች በእንግሊዝ፣ በጣሊያን እንዲሁም በሌሎች አገራት እንደነበሩ ይታወቃል። ለአብነት ያክል የጆፈሪ ቾሰር (1342-1400) “ካንተርቤሪ ቴልስ” (የሕትመት ዘመን በግምት 1387- 1400)፣ የዳንቴ አሊጌሪ (1265-1321) “ዘ ዲቫይን ኮሜዲ” (የሕትመት ዘመን በግምት 1309-20)፣ የጂዮቫኒ ቦካቺዮ (1313-75) “ኢል ዴካሜሮን” (የሕትመት ዘመን በግምት 1348-58) የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ስለዚህ በዚህ ረገድ የቀረበው ምክንያት “ዩቶፕያ” ልቦለዳዊ ድርሰት ላለመሆኑ እዚህ ግባ የሚባል ማስረጃ ሊሆን አይችልም።

III

የሤራ ትርክት ድምጸት (Conspiratorial narrative tone)

ሌላው በአንዳንድ ሌሎች ጸሐፍት ዘንድ እንደሚታየው በመስከረም ጽሑፍ ውስጥም ደራሲዋ ካነሳቻቸው ጭብጦችና ሙግቶች በስተጀርባ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነ ሤራ በምዕራባውያን ዘንድ እንዳለ የሚያንጸባርቅ ድምጸት ይሰማል። የመስከረምን የምርምር ማስታወሻዎችና ለትርጉም ስራዋ እንደግርጌ ማስታወሻ ያቀረበቻቸውን ጽሑፎች ያስተዋለ አንባቢ ሊያነሳቸው ከሚችሉ ጥያቄዎች መካከል “ኢትዮጵያ ዩቶፕያ፣ ዩቶፕያም ኢትዮጵያ” ከሆነች፣ ስለምን ከቶማስ ሞር በኋላም ሌሎች ኢትዮጵያን ላለመጥቀስ፣ ብሎም የኢትዮጵያን ስም በማደናገሪያ ከመዛግብቱ ለማጥፋት ፈለጉ? የሚለው አንዱ ይሆናል። በተጨማሪም፣ ያን ያክል ለምዕራባውያን የተረፈ የአኗኗር ዘዴና ፍልስፍና ወዴት ደረሰ? እንደው ትንሽ እንኳን እንጥፍጣፊው ሳይቀር እንዴትና ወዴት እልም ብሎ ጠፋ? የሚሉ ሌሎች ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ከቀደምት ሃያላንና ሥልጡን አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ፐርሺያ (የዛሬዋ ኢራን)፣ በቶማስ ሞር ዩቶፕያ ውስጥ በስሟ እንደተጠቀሰች (ገጽ 44-45) ያስተዋለ አንባቢ፣ የኢትዮጵያን ስም በ“ማደናገሪያ”ና በማምታቻ መሸፈኑ፣ ብሎም የኢትዮጵያዊነቱን አሻራ ጭራሽ ደብዛውን ለማጥፋት ምዕራባውያን ይህንን ያክል ለምን ፈለጉ? ማለቱ የማይቀር ነው። ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ብትሆን ኖሮ ምዕራባውያን ሊያጡ የሚችሉትስ ከቶ ምን ይሆን? ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች ምላሽ የሚሆን ማስረጃ ቢኖር የሴራ ትርክቱን (ኮንስፒረሲ ቲዮሪውን) ለመቀበል ይቀል ነበር። ይህ በሌለበት ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ጥቂት እኛን፣ እኛን የሚሸቱ ታሪኮች ባየን ቁጥር “የኛ ታሪክ ነው፤ ከኛ ወስደውብን ነው” የሚል የ“ትልቅ ነበርን…” ትርክት ምን ያክል ወደፊት ሊያራምደን እንደሚችል ራስን መጠየቅ ግድ ይላል። ምናልባትም ወደ ውስጥ በአጽንዖት መመልከት የሚጠይቀውን ራስን የመፈተሽ ፈተና ለመሸሽ ቀላል መላ እየዘየድን ይሆን?

ጦቢያ ማለት መልካም፤ መልካም ማለት ኢትዮጵያ?

መስከረም “ዩቶፕያ” ለተሰኘው ቃል የተለመደውን no place የሚለውን የግሪክ ፍቺ “የማደናገሪያ ትርጉም” ነው ትለናለች። ለማስረገጥም “ጦቢያ ማለት መልካም ማለት” መሆኑን ከግእዙ ጦብ (መልካም) ከሚለው ቃል ትርጉም ጋር በማሰናሰል እና ከኦሪት ዘፍጥረት ጋር በማጣቀስ አደናጋሪ ላለችው የዩቶፕያ ትርጉም መፍትሄ እንደሆነ ትጠቅሳለች፡፡ በዚህም የተነሳ የሚከተለውን፣ ወደ ድምዳሜ የሚወስድ መንደርደሪያ (syllogism) የሰጠችን ይመስላል፤

“ጦቢያ ማለት መልካም
መልካም ማለት ዩቶፕያ
ጦቢያ ማለት ዩቶፕያ”

ነገር ግን በስምና በተሰያሚው መካከል ተፈጥሯዊ ግንኙነት እንደሌለ ለመረዳት የግድ የስነልሳን ምሁር መሆን ከአንድ አንባቢ አይጠበቅምና፣ ወ/ሮ ጥሩነሽ የሚባሉ ክፉ ሴት እና አቶ መልካሙ የተሰኙ እኩይ ወንድ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ‘ጦቢያ’ ማለት ‘መልካም’ ማለት መሆኑ ዩቶፕያ (ሁሉ ነገር ፍጹም የሆነባት ስፍራ) ከሚለው ሀሳብ ጋር ቢሰምርም፣ ኢትዮጵያ/ጦቢያ ስሟ እንጂ ጦብ (መልካም) አገሪቱ በግብር ጦብ ናት ለማለት እንዴት ማስረጃ ይሆናል? ይሁንና ነጥቤ ኢትዮጵያ መልካም/ጦብ አይደለችም የሚል ክርክር ለማንሳት ሳይሆን በደራሲዋ የቀረበው የጦብ እና የጦቢያ ማስረጃነት ከቃላት ተመሳስሎ በዘለለ ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት ለሚለው ሙግት ሚዛን አይደፋም ለማለት ነው፡፡

መደምደሚያ

እንደ ደራሲዋ/ተርጓሚዋ ሙግት ለእንግሊዝ ስርነቀል ለውጥ ምክንያት የሆነው ዩቶፕያ ሀገሪቱን ለውጦ ዛሬ ላለችበት (በተለይ ገጽ 288-9 ተመልከት) ደረጃ ሲያደርሳት የዩቶፕያ ባለቤት (እንደ መስከረም አተያይ) የሆነችው ኢትዮጵያ ቁልቁል ወርዳ ራሷን እንኳን መመገብ ተስኗት የምዕራባውያንን እጅ እስከመመልከት እንዴት ደረሰች? የሚለው በተለይ በደራሲዋ/ተርጓሚዋ አመክንዮ የረካ አንባቢ ሊያነሳ የሚችለው ጥያቄ ሊሆን ይችላል።

መስከረም በዩቶፕያ ምክንያት በእንግሊዝ የመጣውን ስርነቀል ለውጥ በርካታ ገጾችን ወስዳ በዝርዝር አትታለች። በመሆኑም ለውጦቹ በዩቶፕያ ምክንያት መምጣታቸውን ለማመን ከባድ ባይሆንም ለለውጡ ምክንያት የሆነችው ዩቶፕያ ግን ኢትዮጵያ ለመሆኗ የቀረበው ማስረጃ አጥጋቢም፣ አሳማኝም አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር በዩቶፕያ አማካኝነት በእንግሊዝ የተከሰተው ለውጥ “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” ለሚለው የደራሲዋ/ተርጓሚዋ ዐቢይ ሙግት የሚያበረክተው የማስረጃነት አስተዋጽኦ ምንም ነው ማለት ይቻላል። በአጭሩ መስከረም በእንግሊዝ ስለመጣው ለውጥ የዘረዘረችውን ያህል፣ ተመሳሳይ ጥናትና ምርምር አድርጋ “ዩቶፕያዊ” አኗኗር በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ዘመን እስከዚህ ዘመን ነበር ልትል ይገባል። በርግጥ እጅግ በጥቂቱ፣ የተወሰኑ ቦታዎች ስምና ዘመን ጠቃቅሳለች (ንግሥናን ከክህነት ጋር አስተባብረው/አዋሕደው የያዙትን የእነላሊበላን፣ ይምርሀነ ክርስቶስን፣ ነአኲቶ ለአብን እና የእነቅዱስ ገብረማርያምን ዘመን፤ ገጽ 231-32)። አለበለዚያ ዝርዝር ማስረጃ በሌለበት፣ የቀደመው ዘመን የመጨራረስና የጦርነት ታሪክ እያለ፣ ቶማስ ሞር ዩቶፕያን ለመጻፍ ያነሳሳው አኗኗር በእውኑ የኢትዮጵያ የዚህ ዘመን ታሪክ ወይም አኗኗር ነው/ነበር ለማለት በማይቻልበት ሁኔታ የደራሲዋን/የተርጓሚዋን “ዩቶፕያ ኢትዮጵያ ናት” ድምዳሜ መቀበል እጅግ ከባድ ይሆናል። በአንጻሩ በግርጌ ማስታውሻ እንዲሁም ወደ ኋላ “የትርጉም ሥራና የምርምር ማስታወሻዎች” ተብለው በቀረቡ ሀተታዎች ውስጥ ለድምዳሜ መንገድ በሚከፍት መልኩ “ለመገመት አያስቸግርም” ፣ “ለመረዳት እምብዛም አይከብድም” (የግርጌ ማስታወሻ 91፣ ገጽ 227፣ ገጽ 262 ወዘተ. ተመልከት) መልኩ የቀረቡ ትንታኔዎችን ለመቀበል ከባድ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የደራሲዋ/የተርጓሚዋ የታሪክ እልቅና (authority as historian) በራሱ ጥያቄ ውስጥ ሊገቡ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ ሊሆን ይችላል። ይህ ማለት ግን ደራሲዋ/ተርጓሚዋ የግድ የታሪክ ምሁር መሆን ስለነበረባት ሳይሆን፣ ያነሳችው ሙግት ከሀገር ፍቅርና ሃይማኖታዊ ቅንዓት (patriotism and religious zeal) በዘለለ ተጨባጭ ማስረጃና መረጃ የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ ነው። በመሆኑም እንደማስረጃ የቀረቡት ዝርዝሮች በተጨባጭ ታሪካዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ እውነትን ለሚሹ ትልቅ ቀርነት ያለበት ጽሑፍ ይመስለኛል።

በመጨረሻም፣ የመስከረም የምርምር ማስታወሻ (የትርጉም ስራዋን ማለቴ አይደለም) ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚያበረክተውን ትሩፋት ስመለከት አገሪቱ (ምናልባትም ዓለማችንም ጭምር) ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚራመድ አይመስልም፡፡ የመስከረም የዩቶፕያ “ጥሪ” ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የታቀደ ጥሪ ነው ለማለትም ይከብዳል። ኢትዮጵያ የብዝሃ-ባህልና በተለይም የብዝሃ-ሃይማኖት አገር መሆንዋ እሙን ሆኖ ሳለ፣ “ተዋሕዷዊ” የተሰኘ፣ ሃይማኖትና መንግስትን ያጣመረ፣ አሃዳዊ መንግስትና ስርዓት ዛሬ አገራችንን ቀፍድደው ከያዟት በርካታ ችግሮች ለመላቀቂያ መፍትሄ፣ ለህዳሴዋ መሰረትና፣ ለአገር ግንባታ ዓይነተኛ ሞዴል ነው ብሎ ማሰብ ከባድ ይሆናል እያልኩኝ ሌሎች ይህን የመስከረምን ግሩም የትርጉም ስራና አከራካሪ የምርምር ማስታወሻ እንዲያነቡትና እንዲወያዩበት በመምከር ጽሑፌን እቋጫለሁ።